
ባሕር ዳር:መጋቢት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአማራ ክልል ያለውን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ በተቋሙ የማስተላለፊያ መስመሮች እና የማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አስታወቀ።
በሥራ አስፈፃሚው አቶ ክብሮም ካህሳይ የተመራ የልዑካን ቡድን የባሕር ዳር-ወልዲያ- ኮምቦልቻ ባለ400/230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ያለበትን የግንባታ ደረጃ በመስክ ተገኝቶ ገምግሟል።
ሥራ አስፈፃሚው በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት ተቋሙ በክልሉ አስተማማኝ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
የጉብኝቱ ዋና ዓላማ በክልሉ እየተገነቡ በሚገኙት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ላይ ለሚነሱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ነው።
እንደ አቶ ክብሮም ገለጻ ተቋሙ በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ የክትትልና ድጋፍ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
በመሆኑም ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ እያደረጉ ያሉ ችግሮችን በመለየት በየደረጃው ካሉ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለመወያየት ታቅዷል ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት በግንባታ ላይ የሚገኙት የኃይል ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ ክልሉ በተደጋጋሚ ሲያነሳቸው ለቆዩት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ያስታወቁት።
ይሁንና ፕሮጀክቱ በሚያልፍባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ምትክ መሬት ለሚያስፈልጋቸው የልማት ተነሺ የማኅበረሰብ ክፍሎች አፋጣኝ ምላሽ ሳይሰጥ መዘግየቱ በግንባታ ሒደቱ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ጠቁመው የሚመለከታቸው የመስተዳድር አካላት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ተቋሙ ከካሳ ክፍያ እና ከኃይል አቅርቦት ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ነው አቶ ክብሮም የተናገሩት።
በከፍተኛ ወጪ እየተገነቡ በሚገኙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ እየተፈጸሙ የሚገኙ የሥርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በወሰን ማስከበር ችግሮች ሳቢያ በባሕር ዳር ከተማ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እና የማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራዎችን በታሰበው መልኩ ማከናወን እንዳልተቻለም ነው ሥራ አስፃሚው የገለጹት።
በጉብኝቱ ላይ የተቋሙ የዋና ሥራ አስፈፃሚ አማካሪ አቶ አንዳርጌ እሸቴን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጮች ተገኝተዋል።
የመስክ ምልከታው ዛሬም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን በፕሮጀክቶቹ ግንባታ ዙሪያ ከሚመለከታቸው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
