ወላጆችና መንግሥት ወጪ በመጋራት የመጻሕፍት ችግርን ሊቀርፉ እንደሚገባ ትምህርት ቢሮ ሐሳብ አቀረበ፡፡

140

በአማራ ክልል በሩብ ዓመቱ በትምህርት ተሳትፎና ተደራሽነት ዝቅተኛ አፈጻጸም መመዝገቡ ተገልጧል፡፡
በአማራ ክልል ምክር ቤት የሰዉ ሀብትና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮን የ2012 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም በመገምገም ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር ተወያይቷል። ነሐሴ ወር መጀመሪያ በትምህርት መስኩ ዙሪያ ዉይይት መደረጉን የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው አስተያዬትና ቅሬታዎችን በመውሰድ ችግሮቹን ለመፍታት የሽግግር መመሪያ (ማንዋል) መዘጋጀቱን ገልጧል።
በክረምት ምዝገባ መርሀ ግብር ሀብትና ጊዜን በመቆጠብ የተሠራው የንቅናቄ ሥራ መሻሻሎች የታዩበት ነበርም ብሏል። በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች፣ ባለሀብቶችና ሌላ አካባቢ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች የኢኮኖሚ ችግር ያሉባቸዉ ተማሪዎችን በትምህርት ቁሳቁስ ለመርዳት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል።
የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ እንደሆነ የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው በ2011 ዓ.ም ከ1ኛ አስከ 12ኛ ክፍል ከ50 በመቶ በላይ ዉጤት ያመጡ ተማሪዎች አሀዝ 83 ነጥብ 45 ከመቶ እንደሆነ ገልጧል።
ከመስክ ምልከታው በመነሳት ‹‹የትምህርት ተሳትፎና ተደራሽነት ዝቅተኛ ነው፤ የ2012 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት አፈጻጸሙ 67 ነጥብ 39 ከመቶ ነው›› ብሏል። የትምህርት መሠረተ ልማት አለመሟላትንና በአንድ ክፍል ዉስጥ ከ100 በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸዉን እንዲከታተሉ መደረጋቸውን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው የመጻሕፍት አያያዝና ስርጭት ችግር እንዳለም አመላክቷል።
‹‹የመምህራን ስርጭትና ስምሪት ሰፊ ውስንነት አለበት›› ያለው ቋሚ ኮሚቴው የትምህርት ቤት የግንባታ ጥራት ችግር፤ የተማሪዎች ሥነ ምግባር ጉድለት፤ የቅድመ መደበኛና ልዩ ፍላጎት ትምህርት መሠረተ ልማት አለመሟላት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትና ሌሎች ችግሮችም ተነስተዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) ‹‹የመጻሕፍት አያያዝና አጠቃቀም ችግርን ለመቅረፍ ወላጆችና መንግሥት ወጪ በመጋራት ዋጋ ወጥቶለት በገበያ ቢፈታ የሚል ሐሳብ አለን›› ብለዋል። የመጽሐፍ ስርጭቱ ላይም በ2011 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ማለፊያ ውጤት ዝቅ በማለቱ እጥረት እንዲያጋጥም ማድረጉን አመልተዋል።
ቢሮ ኃላፊው ‹‹በተማሪዎች ሥነ ምግባር በተግባር የሚገለጽ ለውጥ አልታየም፤ በመሆኑም መሥራት ይጠበቃል›› ብለዋል። በቅድመ መደበኛና ልዩ ፍላጎት የተነሱ ችግሮች ትክክል መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር ይልቃል ‹‹የኤሌክትሪክ ኃይል ችግርን በፀሐይ ኃይል በሚሠሩ መሣሪያዎች ለመፍታት እየሠራን ነው፤ የተነሱት ችግሮች ግን እንደ ግብዓት ተወስደዉ የሚሠራባቸዉ ናቸው›› ብለዋል።
ዘጋቢ፡-ኪሩቤል ተሾመ

Previous articleየምርጫ ሕጉን እና የፖለቲካ ፓሪቲዎችን የምዝገባ አዋጅ በመቃወም ሊደረግ የነበረው የርሃብ አድማ ላልተረወሰነ ጊዜ መራዘሙ ተገለጸ፡፡
Next articleርዕሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ እና በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር በክልሉ በተመድ የሕጻናት መርጃ ድርጅት ድጋፍ የተሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶ ውይይት አደረጉ፡፡