
ባሕር ዳር:መጋቢት 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት እና ፈረንሳይ ጋር የ32 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ተፈራርማለች፡፡
ስምምነቱን የገንዘብ ሚንስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ፣ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ቫለሪ ቴሂዮ እና የአውሮፓ ሕብረት ትብብር የኢትዮጵያ ኃላፊ ስቴፋን ሎክ ተፈራርመውታል፡፡
ድጋፉ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ለግብርና ማገገሚያ የሚውል መሆኑን የሚንስቴሩ መረጃ ያመላክታል።
ፕሮጀክቱ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አማካኝነት የሚተገበር ሲሆን፥ አርሶ አደሮች የግብርና ሥራቸውን ዳግም እንዲጀምሩና የመሰረተ ልማት አገልግሎቶችን ዳግም ሥራ ለማስጀመር ይውላል ነው የተባለው።
በድጋፉ የሚተገበረው ፕሮጀክት በእነዚህ አካባቢዎች የግብርና ምርታማነትን ዳግም በማነቃቃት አስቸኳይ ድጋፍ ለሚሹት ጉዳዮች ምላሽ የመስጠት እና በኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የማጠናከር ዓላማን ያነገበ መሆኑ በዚህ ወቅት ተገልጿል።
በሁለት ዙር ለሚተገበረው ፕሮጀክት ማስፈጸሚያም የፈረንሳይ የልማት ኤጄንሲ 18 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም የአውሮፓ ሕብረት 14 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አድርገዋል።
በመጀመሪያው ዙር 533 ሺህ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተሻሻለ የምርጥ ዘር፣ የዶሮ ዝርያዎች፣ የተመረጡ የወተት ላሞችና የርቢ በግና ፍየሎች፣ የአትክልትና አበባ ምርጥ ዘር አቅርቦት እና ለመስኖ ልማት የሚውሉ ውኃ መሳቢያ ፓምፖች ድጋፍ ይደረጋል ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!