ርዕሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ እና በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር በክልሉ በተመድ የሕጻናት መርጃ ድርጅት ድጋፍ የተሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶ ውይይት አደረጉ፡፡

132

በውይይቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የተመድ) የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስተባባሪዎች እና የክልሉ ሴክተር መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
በክልሉ በተመድ የሕጻናት መርጃ ድርጅት የሚሠሩ ሥራዎች በአብዛኛው በካናዳ መንግሥት የሚደገፉ ናቸው፡፡ ድጋፉም ያላቻ ጋብቻን ለማስቀረት፣ ለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ፣ ለጤናና ለመሳሰሉት ሥራዎች ድጋፍ የሚውል ነው፡፡ ይሁን እንጅ በ2008ዓ.ም 201 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ቢደረግም በ2012 ዓ.ም ድጋፉ በ40 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ቀንሶ 162 ሚሊዮን ብር መድረሱ ነው የተገለጸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በሌሎች ሀገሮች በተከሰተው ድርቅ፣ በእርስ በርስ ግጭት ምክንያት በደረሰው መፈናቀል እና ለሌሎች አስቸኳይ ችግሮች በመዋሉ እንደሆነ በውይይቱ ላይ መነሳቱን ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ተመሥገን ገልጸዋል፡፡
ክልሉ ካለው የተሻለ የመልማት አቅም እና ትርፍ አምራችነት አንጻር በሕጻናት መቀንጨር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ያለውን ትክክለኛ የመቀንጨር መጠን በባለሙያ ጥናት መደረግ እንደሚገባውም ነው የገለጹት፡፡ በቀጣይም ድርጅቱ ሴቶች እና ሕጻናት ላይ፣ ያላቻ ጋብቻ፣ የአካባቢ ንጽሕና እና በጤና አጠባበቅ በተለይም ደግሞ ችግሩ ጎልቶ በሚታይባቸው የተከዜ ተፋሰስ ወረዳዎች ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር አንቶይን ሸቭሬር የተመራው ልዑክ የተለያዩ ተቋማትን የሥራ እንቅስቃሴ ይጎበኛል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
የተመድ የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በክልሉ በሚገኙ 30 ወረዳዎች የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ በውይይቱም የውጭ ዜጎች ክልሉን እንዲጎበኙ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

Previous articleወላጆችና መንግሥት ወጪ በመጋራት የመጻሕፍት ችግርን ሊቀርፉ እንደሚገባ ትምህርት ቢሮ ሐሳብ አቀረበ፡፡
Next articleበኢትዮጵያ 60 ወረዳዎች የበረሃ አንበጣ ተከስቷል፤ ተደጋጋሚ የአውሮፕላን ብልሽት ደግሞ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል እንቅፋት ሆኗል፡፡