“የጎርጎራ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የትናንት ታሪክ፣ የዛሬን እድልና የነገ ሕልም ደምሮ የያዘ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

101
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጎርጎራ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የትናንት ታሪክ፣ የዛሬን እድልና የነገ ሕልም ደምሮ የያዘ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
ፕሮጀክቱ ከሶስት ወር በኋላ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ“ገበታ ለአገር” ፕሮጀክት አካል በሆነው ጎርጎራ ጉብኝት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ጎርጎራ ውስጥ ታሪካችን፣እድላችንና ሕልማችን አለ” ብለዋል።
“ትናንት ታሪካችን ነው፤ዛሬ እድልና ነገ ደግሞ በምናብ የምናየው ሕልማችን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎርጎራ ሶስቱን ቁልፍ ጉዳዮች አጣምሮ መያዙን ገልጸዋል።
የጎርጎራ ታሪክ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ መጠበቅ ባለመቻሉ ምክንያት ያለውን “ግርማና መስህብ እያጣ እንደነበር” ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ አማካኝነት ታሪካዊ ስፍራውን ዳግም እንዲወለድና እንዲታደስ በማድረግ ወደ ነበረበት ክብር መመለስ ብቻ ሳይሆን ልቆ መታየትን አሳይተናል ብለዋል።
በጎርጎራ ፕሮጀክት የተከናወነው ስራ የትውልድ መደመርን ያሳየ መሆኑን በመጠቆም።
“ጎርጎራ ትናንት፣ዛሬና ነገን ያስተሳሰረ ድንቅ ስራ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ አምራና በልጽጋ የምትታይበት ቦታ መሆኑንም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ታሪካዊ ከመሆኑ ውጪ ጥራት፣ብዛትና ቴክኖሎጂን በሚገባ ያስተሳሰረ ነው ብለዋል።
“ጎርጎራ ትውልድ በታሪክ ውስጥ ሊሞላው የሚገባውንና የጎደለውን ሞልቶ እንዲሁም የነበረንን ማነጽና ማላቅ እንደሚቻል የታየበት፤የኢትዮጵያን ተስፋዎች፣ሕልሞችና የምኞታችንን ልክ ያመላከትንበት ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ኢትዮጵያውያን ጎርጎራን መጎብኘትና ሌሎች እንዲጎበኙት ማድረግ እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል።
የትኛውም ጎብኚ ጎርጎራን በማየት ያለ ምንም አስረጂ የኢትዮጵያን ታሪክ መማር፣ የኢትዮጵያን ልክ ለማወቅና የኢትዮጵያን ሕልም ለመረዳት እንደሚችል ተናግረዋል።
ጎርጎራ ለትውልድ የሚተላለፍ አኩሪ ስራ መሆኑንም እንዲሁ።
“ገበታ ለአገር” ፕሮጀክት ጎርጎራን ጨምሮ ሌሎች ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶች ውበት እንዲታይና እንዲጎላ ማድረጉን አመልክተዋል።
በቀጣይ ወደ ትግበራ የሚገባው “ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የትናንት ታሪክ፣የዛሬ እድልና የነገ ሕልም በሚያሳይ መልኩ የቱሪዝም ልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያውያን ብዙ እምቅ የቱሪስት ሀብቶች ፈልቅቆ በማውጣትና በመጠቀም ለትውልድ የሚሸጋገር ስራ ማከናወን እንደሚገባቸውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስገነዘቡት።
“ያደጉ አገራት የእድገት ጫፍ ላይ ደርሰው ሀሳባቸው እያረጀ መጥቷል፤ ኢትዮጵያ እያደገች ነው ወደ ነበርንበት ብቻ ሳይሆን ከዛ ባሻገር ወደ መታደስና ሕዳሴ እየመጣች ነው” ብለዋል።
ትውልዱ ይሄንን በመገንዘብ ያማረና ለትውልድ የሚያሸጋገር ስራ በየአካበቢው እንዲሰራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጎርጎራ ፕሮጀክት ያስተላለፉት መልዕክት
Next articleኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት እና ፈረንሳይ ጋር የ32 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ተፈራረመች።