
የመኢአድ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የከ70 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የወከለው አስተባባሪ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ አበበ እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሕብረት ምክትል ሊቀ መንበር እና የኮሚቴው አስፈጻሚ አባል አቶ ገብሩ በርሄ በስልክ እንደተናገሩት 71 የሚሆኑ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ እና ከፓርቲዎች ምዝገባ ሕጉ ውስጥ የሚሻሻሉ እና የሚሰረዙ ያሏቸው አንቀጾች ተለይተዋል፡፡
አዋጁ ማስተካከያ እስኪደረግበት ጊዜ ድረስም በሥራ ላይ እንዳይውሉ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በደብዳቤ ማሳወቃቸውንም ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ሙሉጌታ እና አቶ አቶ ገብሩ ገለጻ ከትናንት ጥቅምት 25/2011 ዓ.ም ከሰዓት ጀምሮ ለ48 ሰዓት ሊደረግ የነበረው የርሃብ አድማ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል፡፡
የርሃብ አድማው የተራዘመው ከከተማ አስተዳደሩ ይሁንታ ባለማግኘታቸው ምክንያት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ ጥያቄ ካስገቡ ጊዜ ጀምሮ የፈቃድም ሆነ የክልከላ ደብዳቤ እንዳልተሰጣቸው አቶ ሙሉጌታ እና አቶ ገብሩ ተናግረዋል፡፡ የርሃብ አድማውን ለማስፈጸም የተመረጡት አስፈጻሚ ኮሚቴዎች በተደጋጋሚ ወደ ቢሮ ቢሄዱም የቢሮ ኃላፊዎች ባለመገኘታቸው ምላሽ አላገኙም፡፡ የርሃብ አድማ ለማድረግ የመረጡትን አራት ኪሎ አደባባይ በሌላ ቦታ እንዲቀይሩ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል፤ ይሁን እንጂ አቋማቸው በመረጡት ቦታ እና ጊዜ ማካሄድ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ለጊዜው በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረ የሠላም መደፍረስ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የደም ልገሳ እና የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹የርሃብ አድማው ላልተወሰነ ጊዜ ቢራዘምም ቢሮክራሲውን ሰብረን እስከምንወጣ ድረስ የምንታገል ይሆናል›› በማለትም ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ሙሉጌታ እና አቶ ገብሩ ገለጻ የርሃብ አድማው በሌላ ጊዜ የሚደረግ ይሆናል፤ ቀን ግን አልተቆረጠለትም፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ