“የልማት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ከአጋር አካላት የሚበጀትን ገንዘብ በአግባቡ መጠቀም ለቀጣይ የጋራ ትብብራዊ ሥራ ወሳኝ ነው” ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው

79
ባሕር ዳር:መጋቢት 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከግብርና ዕድገት ፕሮግራም በተገኘ የበጀት ድጋፍ የሚገነቡ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
የግብርና ዕድገት ፕሮግራም ፤ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የግብርና ግብዓትን ማሟላት፣የአርሶ አደሮችን የነፍስ ወከፍ ገቢ ከፍ ማድረግ እና የተመጣጠነ የሥርዓተ ምግብን ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ፕሮግራም ነው፡፡ በግብርና ዕድገት ፕሮግራም በ2015 ዓ.ም ማጠናቀቂያ በዕቅድ የተያዙ የመስኖ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም መዘግየት መሠረታዊ ችግር እንደኾነም ተገልጿል።
በውይይቱ ላይ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) እንዳሉት መልማትና መለወጥ የማኅበረሰባችን የህልውና ጉዳይ ኾኖ እያለ በጀትን በአግባቡ ተጠቅሞ የልማት ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸውን ልክ አለማጠናቀቅ ግን ሊያሳስበን ይገባል ብለዋል።
በ2015 ዓ.ም በግብርና ዕድገት ፕሮግራም የበጀት ድጋፍ የሚሠሩ መጠናቀቅ የነበረባቸው 17 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች አሉ ነው ያሉት ኀላፊው።
“የልማት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ከአጋር አካላት የሚበጀትን ገንዘብ በአግባቡ መጠቀም ለቀጣይ የጋራ ትብብራዊ ሥራ ወሳኝ ነው” ያሉት ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው የቀደሙ የልማት ሥራዎች አፈጻጸም ለቀጣይ ሥራ መሰረት ነውና በብቃት የመፈጸም አቅምን በውይይትና በግምገማ ማዳበር እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በመስኖ ልማት ከግብርና ዕድገት ፕሮግራም ጋር በመተባባር በርካታ ሥራዎችን እንዳከናወነ አስታውቋል።
በፕሮግራሙ 513 የመስኖ አውታሮች ተግንብተዋል፣13 ሺህ ሄክታር መሬትም በመስኖ ማልማት መቻሉን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በ2015 ዓ.ም መጠናቀቅ የነበረባቸው እና የዘገዩ 17 የመስኖ ፕሮጀክቶችን እስከ ቀጣይ ሰኔ ወር እንዴት ሠርቶ ማጠናቀቅ እንደሚቻልም ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
በውይይቱ ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች አለመጠናቀቅ የፕሮጀክት አመራር ችግር፣የግንባታ ጥራት ችግር፣ፕሮጀክቶቹ በሚገነቡበት አካባቢ የኀብረተሰቡ የባለቤትነት ግንዛቤ እጥረት እና ተቋራጮች ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ልክ አለመሥራታቸው በተግዳሮትነት የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።
ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየውሻ እብደት በሽታን በማስከተብ መከላከል እንደሚገባ የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
Next articleየማንነት ጥያቄ