የውሻ እብደት በሽታን በማስከተብ መከላከል እንደሚገባ የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

82
ባሕርዳር: መጋቢት 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የውሻ እብደት በሽታን ለመከላከል የሚያስችል የአሠልጣኞች ሥልጠና እየሠጠ ነው። የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጋሻው ሙጨ (ዶ.ር) የውሻ እብደት በሽታን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ ማኅበረሰቡን ከስጋት ነጻ ማድረግ ተገቢ መኾኑን ተናግረዋል። በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ከ55 ሺህ በላይ ውሾችን መክተብ መቻሉ በስልጠናው ላይ ተነስቷል።
ክትባቱን በተመለከተ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ጉዳዩን ተጨባጭ ማድረግ ተገቢ መኾኑንም ዶክተር ጋሻው አንስተዋል። ማኅበረሰቡም ውሻውን በጊዜ በማስከተብ ሊከሰት የሚችለውን ችግር መቅረፍ እንዳለብት ተናግረዋል። ችግሩን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል። የክትባት አቅርቦት በተገቢው መጠን አለማግኘት፣ የባለሙያው የደኅንነት ጥያቄ መኖር፣ ክትባቱ በክፍያ መኾኑ፣ ማኅበረሰቡ ለማስከተብ ፍላጎት አለመኖር ዞኖች እና ወረዳዎች ሥራውን በውጤታማነት ላለመፈጸማቸው በምክንያትነት ተነስቷል።
የውሻ እብደት በሽታ ገዳይ እና አሰቃቂ በሽታ ነው። በሽታው ከእንስሳት ወደ ሰዎች በቀላሉ የሚተላለፍ መኾኑ ችግሩን ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት። ውሻ ከሰዎች ጋር የቀረበ ግንኙነት ስላላቸው በሽታውን በዘላቂነት ለመከላከል አስቸጋሪ ኾኖ መቆየቱ ነው የተገለጸው።
በግብርና ሚኒስቴር የቬተርነሪ ፐብሊክ ሄልዝ ኀላፊ ሲሳይ ጌታቸው (ዶ.ር) በውሻ ላይ ተገቢ ቁጥጥር በማድረግ የውሻ እብደት በሽታን መከላከል ተገቢ መኾኑን አንስተዋል። ችግሩን ለመቅረፍ የሕዝብ ንቅናቄ ሥራን በመሥራት እና ውሾችን በማስከተብ በሽታውን መከላከል እንደሚገባም አስረድተዋል። ባለቤት የሌላቸው ውሾች በሽታውን በማዛመት በኩል ከፍተኛ ድርሻ ይወስዳሉ ያሉት ዶክተር ሲሳይ ማኅበረሰቡ ባለቤት የሌላቸውን ውሾች ምግብ ከመስጠት መቆጠብ እንዳለበትም አሳስበዋል።
የክትባት ሥራው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመኾኑ መንግሥት ሀብት በመመደብ ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዶክተር ሲሳይ ሥልጠናው ሲጠናቀቅ መጋቢት 27/2015 ዓ.ም ውሾችን የመከተብ ሥራ በባሕር ዳር እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ስልጠናው ውሾችን በማስከተብ እኤአ በ2030 የውሻ እብደት በሽታን ከሀገራችን እናጥፋ በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ ነው።
ዘጋቢ :-ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኤርትራ መከላከያ ሰራዊት የጦር ጀነራሎች መኮንኖች የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎበኙ።
Next article“የልማት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ከአጋር አካላት የሚበጀትን ገንዘብ በአግባቡ መጠቀም ለቀጣይ የጋራ ትብብራዊ ሥራ ወሳኝ ነው” ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው