
ባሕር ዳር:መጋቢት 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጊቤ ሁለት የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የጥገና ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሹመት በላቸው አስታወቁ።
ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት የጥገና ሥራው በዋናነት እየተከናወነ የሚገኘው ዩኒቱን በአውቶማቲክ ሲስተም የመቆጣጠሪያ ዘዴ እንዲሰራ ለማድረግ ነው።
የጥገና ሥራው የሚከናወነው የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ካሉት አራት ተርባይኖች ውስጥ በአንደኛው ዩኒት ውኃን በተፈለገው መጠን ወደ ተርባይን ለማስተላለፍ በሚያገለግሉት ሹል ጫፍ ባላቸው ስድስት የፓወር ኖዝሎች ላይ ብልሽት በማጋጠሙ እንደሆነ ነው አቶ ሹመት የተናገሩት።
የፓወር ኖዝሎቹ ውስጥ ያሉት ክፍሎች በመጎዳታቸው ሳቢያ የኃይል ማመንጫ ዩኒቱን የማመንጨት አቅም በተፈለገው መጠን በአውቶማቲክ ሲስተም መቆጣጠር እንዳልተቻለም ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት ጉዳት የደረሰባቸውን ስድስት የፖወር ኖዝሎች የውስጥ ክፍሎች በአዲስ የመቀየር ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
በውስጡ የሚገኙት ሲሊንደሮች ላይ የዘይት መፍሰስ ችግር እንዳያጋጥም የሚከላከሉ አካላትን (Sealers) በአዲስ የመቀየር ሥራም እየተከናወነ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
እየተከናወኑ የሚገኙት የጥገና ሥራዎች ሲጠናቀቁና ዩኒቱ ዳግም ወደ ሥራ ሲመለስ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ሹመት ገለፃ በጣቢያው እየተከናወኑ የሚገኙትን የጥገና ሥራዎች ከ15 ቀናት ባነሰ ጊዜ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙንም ተናግረዋል።
ለጥገና ሥራው የሚያስፈልጉ አንዳንድ የመለዋወጫ ዕቃዎች ላይ ማሻሻያ በማድረግና የሞዲፊኬሽን ሥራ በመስራት ተቋሙን ከተጨማሪ ወጪ መታደግ እንደተቻለም ነው ሥራ አስኪያጁ የገለጹት።
የጥገና ሥራው ከጣቢያው፣ ከተለያዩ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችና ከማዕከል በመጡ የተቋሙ ሠራተኞች እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት።
የጊቤ ሁለት የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በ2002 ዓ.ም ተመርቆ በይፋ ሥራ የጀመረ ሲሆን እያንዳንዳቸው 105 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው አራት ዩኒቶች ያሉትና በድምሩ 420 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!