
አዲስ አበባ:መጋቢት 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ምስረታ በአዲስ አበባ ሲካሄድ በመድረኩ የተገኙት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ምስረታ ወጣቶች በመረጡት ሕጋዊና መሠረታዊ አደረጃጀት ተደራጅተው ድምጻቸውን እንዲያሰሙ፣ የራሳቸውን ጥያቄ ራሳቸው እንዲያነሱና ችግሮቻቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ሚንስትሯ ወጣቶች በተናጠል ሊፈጽሟቸው የማይችሏቸውን ተግባራት በጋራ እንዲከውኑ የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠራቸው ውጤት እንደሚኖረውም ነው ያስረዱት።
በአህጉራዊና ዓለማቀፋዊ መድረኮች ኢትዮጵያን የሚወክል አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ ሆኗል ያሉት ሚኒስትሯ ለዚህ ሀገራዊ የወጣቶች ምክር ቤት መንግሥት በመርህ ላይ የተመሠረተ ማናቸውንም ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። “ወጣቶች በመንግሥትና በሀገሪቱ መካከል ድልድይ እንድትሆኑ አሳስባለሁ”ብለዋል። ሚንስትሯ በወጣቶች የሥራ ፈጠራ ላይ ምክር ቤቱ በትኩረት እንዲሠራም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክርቤት ፕሬዚዳንት ወጣት ፉአድ ገና ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ከፍታ ወጣቶችን አስተባብሮ ይሠራል ብሏል። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲዳብርና የወጣቶች ጥያቄዎች እንዲመለሱና ለሰላምና ደኅንነት መከበር ይሠራል ያለው የምክር ቤቱ ፕሬዝደንት ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ድምጽ ለመሆን አበክሮ እንደሚሠራ ተናግሯል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚንስቴር ዓለሙ ስሜ (ዶ.ር) ምሥረታውን አስመልክተው እንዳሉት ወጣትነት ትኩስ ኀይል ፣ዕምቅ አቅምና የለውጥ ፍላጎት ያለበት የዕድሜ ክልል መሆኑን አንስተው ይህንን ኃይል በአግባቡ መምራት ይገባል ብለዋል።
ይህንን የወጣቱን ኀይል ከብሔር ልዩነት ተሻግሮ የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ከሚጎዳ ነገር አርቆ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚሠራ እንዲሆን ይጠበቃል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ምስረታ “የወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግስቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!