“ባለግርማው ደብር፣ በጎጃም ሰማይ ሥር”

138
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የተባረከ ምድር መልካም ዘር ይበቅልበታል፣ የተባረከ ምድር ታሪክ ይሠራበታል፣ የተባረከ ምድር ሃይማኖት ይፀናበታል፣ የተባረከ ምድር ጥበብ ይፈልቅበታል፣ በተመረጠ ምድር አበው በቅድስና ይኖሩበታል፣ እመው በትሕትና ይመላለሱበታል። ገዳማት ተገድመውበታል፣ አድባራት ተደብረውበታል፣ ሊቃውንት መልተውበታል።
የተባረከች ምድር ፈጣሪዋን ታስባለች፣ የተባረከች ምድር ትእዛዛትን ታከብራለች፣ የተባረከች ምድር ሕግና ሥርዓትን ታፀናለች፣ በሕግና በሥርዓት ትገዛለች፣ አምላኳን እያመሰገነች፣ ከአምላኳ በረከት ትቀበላለች ፣ በበረከትም ትኖራለች። የታደለች ምድር መልካሙን ሁሉ ትይዛለች። የተባረከች ምድር ሕዝብን ሁሉ ትሰበስባለች፣ በአንድነት ታጸናለች። የተባረከ ምድር፣ ሁሉን የሚሰጥ አፈር፣ ሁሉ የሚገኝበት፣ በረከት የበዛለት፣ ረድዔት የማይለይበት፣ አንዲት የሥንዴ ዘለላ ብዙ ኾና የምትነሳበት፣ ነጭና ጥቁር የሚበቅልበት፣ ወተትና ማር የመላበት፣ ደጋጎች የሚኖሩበት። ቅኔ የሚዘረፍበት፣ ሊቃውንት የሚፈልቁበት፣ ደቀመዛሙርት የሚሰባሰቡበት።
ገበሬዎች ሳይሰለቹ ያርሳሉ፣ በተባረከው ምድር ላይ ዘራቸውን ይበትናሉ፣ በሰፊ አውድማ ላይ ነጭና ጥቁር ያፍሳሉ፣ በበሬዎቻቸው እሸት፣ በላሞቻቸው ወተት እየሰጡ ሀገሬውን ከዓመት እስከ ዓመት ይመግባሉ። ሊቃውንቱ ቀለም በጥብጠው፣ ብራና ፍቀው ታሪክ ያስተምራሉ፣ ሃይማኖት ያፀናሉ፣ ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን ያሳያሉ። በምስጢር ይራቀቃሉ፣ በጥበብ ይረማመዳሉ። እንደ ዥረት እያረሰረሰ ከሚወርደው የቅኔ ጥበብ ያጠጣሉ፣ እውቀት የተጠማን ያረካሉ፣ ጥበብ የተራበን ይመግባሉ። በጥበብና በትሕትና ያጎናፅፋሉ።
በዚያ ምድር ከጠቢበኞች ጋር ጀግኖች ይኖራሉ። ጠቢባን ጥበብን ያስተምራሉ፣ ጀግኖች በጀግንነት ሀገር ይጠብቃሉ፣ ወሰን እና ድንበር ያስከብራሉ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋን የኢትዮጵያ ሠንደቅ ከእነክብሯ ትኖር ዘንድ ደም ያፈስሳሉ፣ አጥንት ይከሰክሳሉ። በዚያ ምድር ሴቶችም፣ ወንዶችም ቅኔ ይዘርፋሉ፣ በምስጢር ይራቀቃሉ። ወንበር ተክለው ለደቀመዛሙርቱ የተወደደውን ያስተምራሉ። ደጋጎቹ ስሞት አፈር ስሆን እያሉ ያጎርሳሉ፣ ከፍርንዱሱ ያጠጣሉ። ደጋጎች የበዙበት፣ ጀግኖች፣ አስተዋዮች፣ ልበ ሙሉዎች የሚወለዱበት ጎጃም።
አእዋፋት መዘመር ጀምረዋል። ጨለማ ስልጣኑን እያስረከበ ነው። የብርሃን ፀዳል በምድር ላይ ማንዣበብ ጀምሯል። ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ ለምስጋና የቆሙ ካህናት እና ዲያቆናት በአሻገር ሲዘምሩ ይሰማሉ። ጥዑመ ዜማቸው ለነብስ ሀሴትን ትሰጣለች። ኑ ቅረቡ ታሰኛለች። የታደሉት ለምስጋና ቆመው ያድራሉ፣ ለምድር እና ለሰዎች በረከትን ይለምናሉ። ፅድቅ እንድትቀርብ ኩነኔ እንድትርቅ ይማፀናሉ። ለአምላካቸው ይሰግዳሉ። ስጋቸውን እያደከሙ ነብሳቸውን ያጠነክራሉ፣ ለማታልፈዋ ዓለም ያዘጋጃሉ። ቅደሜ ለእሁድ አጥቢያ ነበር። በዚያች ማለዳ ወደ አንድ ታላቅ ሥፍራ እሄድ ዘንድ ቀጠሮ ይዤያለሁ። እሄድበት ዘንድ ቀጠሮ የያዝኩበት ሥፍራ ከስም አጠራሩ ጀምሮ አስቀድሞ አጓጉቶኛል።
የካህናቱን እና የዲያቆናቱን ዝማሬ በአሻገር እየሰማሁ ከአልጋዬ ተነሳሁ። የታደሉት እንቅልፍ ትተው ለምስጋና ቆመው አድረዋል። እኔ ግን በማለዳ እንኳን ለመነሳት ብዙ ጊዜ ቆየሁ። ስንፍናዬ ታገለችኝ። ዳሩ ከዚያ ሥፍራ እቀር ዘንድ አልወደድኩምና እንደምንም ተነሳሁ። ቸር ያሳደረ አምላክ ቸር ያውለኝ ዘንድ አደራውን ለእርሱ ሰጥቼው ከቤቴ ወጣሁ። በአሻገር ሲሰማኝ ወደ ነበረው የካህናት ዜማ ቀረብኩ። ነጫጭ የለበሱ ምዕመናን በማለዳ ተነስተው በአጸዱ ሥር ለምስጋና ቆመዋል። በአጸዱ ሥር ተጠልለዋል። በማለዳ ተነስተው በአጸዱ ሥር ለምስጋና የቆሙትን፣ ከቤታቸው ተነስተው ለምስጋና ወደ አጸዱ ሥር የሚጓዙትን በትዝብት እያየሁ ወደ ፊት ተጠጋሁ።
አየው ዘንድ ወደ ጓጓሁለት የሚወስዱኝ መኪናዎች ምዕመናን በሚሰባሰቡበት አጸድ አጠገብ እንደሚገኙ አስቀድሜ ሰምቻለሁ። መኪናዎች በጠዋት ተደርድረዋል። ወደዚያ ሥፍራ የሚጓዙ ሰዎች በሥርዓት ወደ መኪናዎቹ ይገባሉ። እኔም እንደሌሎቹ ሁሉ በአንደኛው መኪና ውስጥ ገብቼ ተቀመጥኩ። ደቂቃዎች ቆጠሩ። የመኪናዎቹ መንቀሳቀሻ ሰዓት ደረሰ። በመኪናው ውስጥ ያሉ ሰዎች መንገዳቸው የቀና ይሆን ዘንድ ከመቀመጫቸው ተነስተው በአድነት አምላካቸውን አመሰገኑ። መኪናዎች መንቀሳቀስ ጀመሩ። ፊታቸውን ከባሕርዳር ወደ አዴት መሥመር አዙረው ተምዘገዘጉ። ዓይኔ ቀኝና ግራውን እያማተረች ጉዞው ቀጠለ። መንገዱ ረጅም አይደለም። ከባሕርዳርም እምብዛም አይርቅም። ከመጓጓቴ የተነሳ መዳረሻ ከሆነው ሥፍራ ራቀብኝ። መኪናዎች በከነፉ ቁጥር ያን ሥፍራ የማየት ጉጉቴ ጨመረ።
ጉዟችን ቀጥሎ በታላቋ ደብር በደብረ መዊ ማርያም ስም በተሰየመችው ደብረ መዊ ከተሰኘችው ትንሽዬ ከተማ ደረስን። ደብረ መዊ ማርያም የከበረ ታሪክ ያለባት ታላቅ ሥፍራ ናት። መዳረሻችን ከደብረ መዊ ባሻገር ከሚገኝ ታላቅ ሥፍራ ነው። መኪናዎች የአስፓልቱን መንገድ ትተው ወደ ምሥራቅ ንፍቅ ታጥፈው ወደ ውስጥ ገቡ። ጥቂት እንደተጓዝንም ልቤ ሲጓጓለት ከነበረው ሥፍራ ደረስን። ዙሪያ ገባው የተዋበ፣ ረጃጅም ፅዶች የከበቡት፣ እርጋታ ያለበት፣ ግርማ የበዛበት ታላቅ ሥፍራ። ይህ ሥፍራ በጎጃም ሰማይ ሥር በይልማና ዴንሳ ይገኛል።
May be an image of outdoors
ግርማውና ውበቱ እያስደነቀኝ በዝግታ ወደ አጸዱ ተጠጋሁ። ዙሪያውን የከበቡት እድሜ ጠገብ ዛፎች ለምስጋና የቆሙ ይመስላሉ። ወደ ውስጥ በተጠጉት ቁጥር ማዕዛው ይጣራል። ኑ ከአጸዱ ሥር ተጠልላችሁ ኑሩ ይላል። አበጥራር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን። አንዳንዶች ደግሞ አበጥራ ይሉታል። በአጸዱ ዙሪያ እየተመላለስኩ ተመለከትኩት። ባየሁት ሁሉ ተገረምኩ። አበው ስለ ስያሜው ሲናገሩ ጥራር ማለት የጦር መከላከያ ልብስ ማለት ነው። አበ ማለት ደግሞ አብ አባት ማለት ነው። ይህም አበጥራር ማለትም የአባት መከላከያ ልብስ ማለት ነው ይላሉ። በዚያ ደብር ሲያገለግሉ የኖሩት መጋቢ አምሳሉ ዳምጤ ደግሞ ስለ ስያሜው ሲነገሩኝ ሦስት ባሕታውያን መጡ። ሦስቱም አምላክ በፈቀደላቸው ሥፍራ ተቀመጡ። አበጥራር ጊዮርጊስን የተከሉት ባሕታዊው አደራ ማርያም ይባላሉ። እሳቸውም አበጥራር በተሠራበት ተቀመጡ። ሌላኛው ባሕታዊ ፈረስ ወጋ አለፍ ብላ በምትገኝ አኔር ማርያም በተሰኘች ሥፍራ ተቀመጡ። ሦስተኛው ባሕታዊ ደግሞ በሜጫ ተቀመጡ። እነዚህ ባሕታውያንም አምላክ በፈቀደላቸው ባዕት ሆነው ሱባዔ ያዙ። እንዲህም ኾነው ለዓመታት ኖሩ። ከዓመታት በኋላም አደራ ማርያም የተሰኙት ባሕታዊ አኔር ማርያም ወደ ሚገኙት ባሕታዊ ሄዱ። በዚያም ተገናኙ። ስለ አከራረማቸውም ተጠያየቁ። ሱባዔ ይዘው የኖሩበትን ሥፍራም አዩ። ወደሌላኛው ባሕታዊ ሥፍራም ሄደው በዓታቸውን አዩ። በኋላም አደራ ማርያም የነበሩበትን በዓት አሳዩን አሏቸው። ሦስት ኾነውም ወደዚያ ሥፍራ መጡ። ሥፍራውን ባዩት ጊዜም ያማረ ነበር። በአራቱም ንፍቅ የተመቻቸ ነውና” እርስዎማ የተበጠረውን ሀገር አይደል ያገኙት”አሏቸው። የተበጠረ ማለት ያማረ፣ የተዋበ፣ ጉድፍ የሌለበት ማለት ነው። በዚህም የተነሳ አበጥራ፣ አበጥራር ተባለ ነው ያሉኝ። ገሚሶቹ አበጥራር ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ አበጥራ ይሉታል።
ጥንታዊው እና ባለ ግርማው ደብር መቼ እንደተደበረ በውል ለማወቅ አስቸጋሪ ነው ይሉታል። ደብሩ የተደበረበትን ዘመን ባነሱም ጊዜ አበጥራር በሠይፈ አርድ ዘመነ መንግሥት ተመሠረተ ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ በዘመነ መሳፍንት ስማቸው ጎልቶ በሚነሱት በስዑል ሚካኤል ነው የተደበረውም ይላሉ። የታሪኩ ጥንታዊነት ግን በሠይፈ አርድ ዘመን ሳይደበር እንዳልቀረ ነው የሚነገረው። በዚህ ዘመን ገዳማት ይገደሙ አድባራት ይደበሩ ነበር። በዚያ ዘመን በቅዱሳን አበው ከተደበሩ አድባራት መካከል የተደበረ ሳይሆን እንዳልቀረ ይነገራል።
ይህ ጥንታዊ ደብር በጥንት ዘመን በገዳማዊ ሥርዓት ይተዳደር እንደነበርም ይነገራል። ገዳሙ ሲገደምም በሦስት ጽላቶች ተገደመ ይባላል። በዚህ ደብር ጥንታዊ ምስክር የሚሆኑ በጦር አበጋዞች የተሰጡ ስጦታዎች ይገኛሉ። አበጥራር ጊዮርጊስ ኪዳን እየተደረሰበት፣ ቅዳሴ እየተቀደሰበት፣ ስጋ ወ ደሙ እየተፈተተበት ለዘመናት ቆዬ። በመካከል ግን የመከራ ዘመን መጣ ይላሉ አበው። ያም የመከራ ዘመን መቼ እንደሆነ በውል ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ያ የመከራ ዘመን ጥንታዊው ደብር እንዲጠፋ አደረገው። ቤተክርስቲያኑ ጠፍቶ በነበረበት ጊዜም የሀገሬው ሰው አጸዶቹን እና ሌሎች ዛፎችን ሲጥብቅ ኖሯል። ፈቃደ እግዚአብሔር እስኪደርስ ድረስ በክብር አቆይቷል። ፈቃደ እግዚአብሔር በደረሰ ጊዜም ደብሩን ደበሩ። ቅዳሴ ቤቱን አከበሩ። በመከራው ጊዜ ጠፍቶ በነበረበት ጊዜ በዚያ ቅዱስ ሥፍራም የበቁ አባቶች ይኖሩበት፣ በቅድስና ይመላለሱበት ነበር ይባላል። ሥፍራው እጅግ የተከበረ፣ በመካከሉ እንደተፈለገ የማያንቀሳቅስ ደን እንደነበርም መጋቢ ነግረውኛል።
ዘመን ዘመንን አስከተለ። ፈቃደ እግዚአብሔር ደረሰ። በዚያ ዳግም ኪዳን ሊደረስ፣ ቅዳሴ ሊቀደስ። መጋቢ አምሳሉ ዳምጤ እንደነገሩኝ ለዓመታት ጠፍቶ ከኖረ በኋላ በአምላክ ፈቃድ በ1970 ዓ.ም ደብሩ ተደበረ። በሚያዚያ 23 ቀን በ1970 ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ።
ከዓመታት በኋላ ቤተ መቅደሱ በታነፀ ጊዜ መሥሪያ እንጨት አጣን ይላሉ አበው። “ምን ተሻለን ብለን መከርን። የግድግዳ እንጨት አጣን። በስሚዛው ጨፍቀን እንቆይ እንጂ አልን። ከዚያም በአንድ ቀን ደመና ድንገት በደብሩ አናት ላይ ሲቋጠር ተመለከትኩ። ዝናብ ሊመጣ ነው እንዴ አልኩ። ድንገት መብረቅ ጓጓ ብሎ ጮኸ። መብረቁ በደብሩ አጠገብ ያለውን አንዱን ፅድ መታው። ቅጠሉ ከካቡ ውጭ ረገፈ። ጽዱ እየተፈለጠ ወደ ካቡ ውስጥ ገባ። በመጥረቢያ የተፈለጠ ይመስላል። የእርሱ ፈቃድ መሆኑን ተረዳን። በስሚዛ የተጨፈቀውን እያወጣን ፍልጡን ማቆም ጀመርን። በመብረቅ ተመትቶ የተፈለጠው የጽድ እንጨት ረዝሞም አልተቆረጠም። አጥሮም አልተቀጠለም። ጎድሎም አልታከለም። በዝቶም አልተረፈም። ሁሉም ልክ ሆኖ ገጠመ እንጂ። መጥረቢያ አልነካንም። እርሱ በፈቃዱ አስተካከለው እንጂ” ነው ያሉኝ መጋቢ።
አበው በመብረቅ ተመትቶ የተፈለጠውን ጽድ አሳይተውኛል። ሌላ አንድ ጥንታዊ ጽድ ከእድሜ ብዛት ለመውደቅ ዘመመ። የዘመመውም ወደ ቤተመቅደሱ ነበር። ቤተመቅደሱ ይመታል ብለን ፈራን። ኋላ ግን ወደ ሌላ ቦታ ዞሮ ወደቀ። ይህም ጽድ ታሪክ እየመሠከረ ዛሬም ድረስ አለ። ባሕታዊያን ይኖሩበት፣ ጳጳሳት ሱባዔ ሲይዙበት የኖረ ታላቅ ደብር። ግርማው፣ ጸጥታው ሁሉ አጀብ ያሰኛል። በረጃጅም ጽዶች ሥር ተቀምጬ በዝምታ ተመለከትኩት አጀብ ያሰኛል። በጥበብ የተሠራው የቅጽሩ ውበት ቀልብ ይስባል። በዚያ አጸድ ሥር ታሪክ የሚነገርባቸው፣ ሃይማኖት የሚሰበክባቸው፣ በረከትና ረድዔት የሚገኝባቸው የከበሩ ንዋዬ ቅድሳት መልተዋል።
ዓይኔ መልካሙን ነገር አየች። እግሬ በተቀደሰው ሥፍራ ተመላለሰች፣ አፍንጫዬ ከማዕዛዎች ሁሉ የላቀውን ማዕዛ አሸተች፣ እጄም ቅዱሱን ሥፍራ ዳበሰች፣ ጀሮዬም የተወደደውን ድምፅ ሰማች፣ ትእዛዛትን አደመጠች፣ ልቤ ባየችው ነገር ሁሉ ሀሴትን አደረገች። ወደዚያች ሥፍራ ሂዱ መልካሙን ነገር ታያላችሁ፣ በአጸዱ ሥር ተመላለሱ ሀሴትን ታገኛላችሁ፣ የከበረውን ማዕዛ ታሸታላችሁ፣ ታሪክ ትማራላችሁ፣ ጥብብን፣ መወደድን እና ግርማን ታያላችሁ።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ቡሬ ከተማ ላይ መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ የሚመጣ ባለሃብት ጊዜ የሚፈጅበት እና የሚጉላላበት አሠራር የለም” ከተማ አሥተዳደሩ
Next articleበቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚከናወኑት ጨዋታዎች ዙሪያ ያልዎትን ግምት ይስጡ!