“ቡሬ ከተማ ላይ መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ የሚመጣ ባለሃብት ጊዜ የሚፈጅበት እና የሚጉላላበት አሠራር የለም” ከተማ አሥተዳደሩ

157
ፍኖተ ሠላም:መጋቢት 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቡሬ ከተማ በአማራ ክልል የኢንዱስትሪ መንደር ካላባቸው ከተሞች መካከል አንደኛዋ ናት። ከተማዋ ለሀገር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያላቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች የተተገበሩባት እና እየተተገበሩባት ያለች ከተማም ናት። ከተማዋ ለንግድ እና ኢንቨስትመንት የተመቸች በመሆኗ በርካታ ባለሃብቶች ይመርጧታል።
የቡሬ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አበጀ ሙላት ቡሬ ከተማ በጥሩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ገልጸዋል። በከተማዋ መቶ ሰባ የሚሆኑ ባለሃብቶች ቦታ ተረክበው እየሠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ሠላሳ አምስት የሚሆኑ ባላሃብቶች የማምረት ሥራ መጀመራቸውንም ነግረውናል። በከተማዋ መዋዕለ ንዋያቸውን ከሚያፈሱ ባለሃብቶች መካከል ለውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመሩ መኖራቸውንም አስረድተዋል።
ምርት ከጀመሩ ሠላሳ አምስት ፕሮጀክቶች በተጨማሪ አሥራ አራት የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ደግሞ ግንባታቸውን አጠናቀው የመብራት ኃይል በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። አርባ ሁለት የሚደርሱ ፕሮጀክቶችም በግንባታ ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት። የከተማ አሥተዳደሩ ባለሃብቶችን እየደገፈ መሆኑንም አንስተዋል። በከተማዋ ሦስት የኢንዱስትሪ መንደር አለ ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለባለሃብቶች የመሥሪያ ቦታ እየሰጠን ነውም ብለዋል።
May be an image of outdoors
ቡሬ ከተማ ላይ መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ የሚመጣ ባለሃብት ጊዜ የሚፈጅበት እና የሚጉላላበት አሠራር የለም ብለዋል። ባለሃብቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ተቀራርቦ በመሥራት እየደገፉ እንደሆኑም አብራርተዋል። በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ ሃብት ያመነጩ ባለሃብቶችን መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት። ከተማዋ ለንግድ የተመቸች መሆኗንም ገልጸዋል። አካባቢው ትርፍ አምራች በመሆኑ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ለለውጥ በሚያግዙ ዘርፎች ላይ እንዲያውሉ ጠይቀዋል። ከከተማዋ በቅርብ ርቀት የማዕድን ክምችት መኖሩንም አንስተዋል። ባለሃብቶች በፈለጉት የኢንቨስትመንት አማራጮች ኢንቨስት ማድረግ እንደሚችሉም ገልጸዋል። የከተማዋ ማኅበረሰብ ሥራና ልማት ወዳድ በመሆኑ ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ እንደሆነም ተናግረዋል። ባለሃብቶች በቡሬ ከተማ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ራሳቸውን እና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ምስረታ በአዲስአበባ እየተካሄደ ነው።
Next article“ባለግርማው ደብር፣ በጎጃም ሰማይ ሥር”