
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት በልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ 600 ባለሀብቶች የኢንቨስትምንት ፈቃድ መስጠቱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በቢሮው የፕሮሞሽንና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይኼነው ዓለም በክልሉ በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በልዩ ልዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ 554 ባለሀብቶች የኢንቨስትመት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ለ600 ባለሀብቶች ፈቃድ መሠጠቱን ገልጸዋል፡፡
ቢሮው በሩብ ዓመቱ 4 ቢሊዮን 799 ሚሊዮን ብር ካፒታል ለሚያስመዘግቡ ባለሀብቶች ፈቃድ ለመስጠት አቅዶ ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት አቶ ይኼነው ባለሀብቶቹ ከእቅድ በላይ 19 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራት ፈቃድ ከወሰዱ 600 ባለብቶች ውስጥ 124 በግብርና ምርቶች ማቀነባበር፣ 21 በጨርቃ ጨርቅ፣ 57 በቱሪዝም፣ 52 በኬሚካል ማምረት፣ 87 በእንጨትና ብረታብረት፣ 57 በግብርና ዘርፍ እና ቀሪዎቹ ደግሞ በግንባታ፣ በአበባ ልማት እና ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት የወሰዱ ናቸው፡፡ ባለሀብቶቹ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡም ከ60 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡
የክልሉ የኢንቨስትመት እንቅስቃሴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መነቃቃት እያሳየ እና ቆመው የነበሩ ፕሮጅክቶችን ለማጠናቀቅ በባለሀብቶች ዘንድ የተሻለ መነሳሳት የተፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡- የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት