የአማራና የአፋር ክልሎች በሚዲያ አገልግሎት የሚያደርጉትን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግና ለሀገራዊ አንድነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

78
Made with LogoLicious Add Your Logo App
ሰመራ፡ መጋቢት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የአፋር ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ሰነድ በሰመራ ተፈራርመዋል።
ሰምምነቱን የተፈራረሙት የአፋር ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አህመድ ካሎይታ እና የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቦርድ አባል ግዛቸው ሙሉነህ ናቸው።
በሰመራ በተካሔደው የፊርማ ሥነሥርዓት ላይ የአሚኮ እና የአፋር ቴሌቪዥን ሥራ አስፈጻሚዎች ተገኝተዋል።
አቶ አህመድ እንዳሉት የአፋር ሕዝብ ከአጎራባች የአማራ ሕዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል፤ ሁለቱ ሕዝቦች ጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብር አላቸው።
ይህን የሕዝብ ለሕዝብ ጠንካራ ትስስር ደግሞ አመራሩ መደበኛ ተግባሩ አድርጎ መደገፍ ስለሚገባው የዛሬው ስምምነት ዋሳኝ ነው ብለዋል።
ጎንደር እና ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲዎች አፋር ክልል በእውቀት ግንባታ በዘርፉ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ነፃ የትምህርት እድል በመስጠት እያስተማሩ ነው ብለዋል። ይህ ሕዝባዊ ግንኙነቱ ምን ያክል ጠናካራ እንደሆነ ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል።
አፋርኛ ፕሮግራም በአሚኮ መጀመሩ ግንኑነቱን ያጠናክረዋል ያሉት ቢሮ ኃላፊው፤ በአፋር ቴሌቪዥንም የአማርኛ ሥርጭት መጀመሩን ገልጸዋል። ስምምነቱም ከዚህ በፊት የነበረውን ጠንካራ የመረጃ መመጋገብ ተግባር መደበኛ የማድረግ ነው ብለዋል።
አፋር ክልል የሚያከናውነውን የልማት ተግባር ጨምሮ፣ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮዊ ችግሮች ሲያጋጥሙ አሚኮ ቀድሞ የሚዲያ ሽፋን ይሰጥ ነበር፤ ክልሉም ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፤ ይህ የሁለቱ ክልሎች ሁሉአቀፍ መተጋገዝ የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊና የአሚኮ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ግዛቸው ሙሉነህ የሕዝባችንን ኢኮኖሚ ማሳደግ ላይ ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።
ስምምነቱም ሁለቱ ሚዲያዎች እንደ ሁለት መሥሪያቤት ሳይሆን በጠንካራ ትብብር ባሕር ዳር የሚገኝ የአፋር ቴሌቪዥን መሥሪያ ቤት፤ ሰመራ የሚገኝ የአሚኮ መሥሪያ ቤት አይነት በማድረግ የነበረውን የትብብር አሠራር እንዲጠናከር የሚረዳ ነው ብለዋል።
ስምምነቱ ጠንካራውን የአፋር እና አማራ ሕዝብ ወንድማዊ አንድነት በሚዲያ በኩል ለማገዝ ዓላማ ያለው ነው።
ዘጋቢ ፦ አንዷለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleመንግሥት በጥጥ ምርት የተፈጠረውን የገበያ ችግር እንዲፈታላቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ጠየቁ።
Next articleየወፍላ፣ ኮረምና ዛታ ነዋሪዎች ማንነታቸው እንዲከበር የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄዱ ነው።