መንግሥት በጥጥ ምርት የተፈጠረውን የገበያ ችግር እንዲፈታላቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ጠየቁ።

159
ገንዳ ውኃ፡ መጋቢት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በ2014/15 የምርት ዘመን ከፍተኛ የጥጥ ምርት ቢመረትም አርሶ አደሮች የገበያ ችግር እንደገጠማቸው ለአሚኮ ተናግረዋል።
ገዥ ያጣው የጥጥ ምርት አሁንም ድረስ ከማሳ ላይ አልተሰበሰበም። በአማራ ክልል ገበያ ተኮር አምራች ከኾኑ አካባቢዎች ምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው።
ጥጥ ደግሞ በአካባቢው በስፋት ከሚመረቱት ምርቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው።
በ2014/15 የምርት ዘመን በአካባቢው ከፍተኛ የጥጥ ምርት ቢመረትም አርሶ አደሮችን የገበያ ችግር ገጥሟቸዋል።
የገበያ ችግር ካጋጠማቸው አርሶ አደሮች መካከል አቶ አበጀ ስንለው አንዱ ናቸው። አቶ አበጀ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ በምዕራብ ጎንደር ዞን በእርሻ ልማት ተሠማርተዋል።
በ2014/15 የምርት ዘመን በዞኑ ምዕራብ አርማጭሆና ሌሎች ወረዳዎች አኩሪ አተር፣ ማሾና ጥጥ በስፋት አምርተዋል። በምዕራብ አርማጭኾ ወረዳ ብቻ 160 ሄክታር መሬት የጥጥ ምርት አምርተዋል።
ከዚህም እስከ 1 ሺህ 800 ኩንታል ጥጥ እንደሚያገኙ ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ እንዳሉት በ2014/15 የምርት ዘመን ከ2013/14 የምርት ዘመን በተሻለ የጥጥ ምርት ቢመረትም በገበያ ማጣት ምክንያት ኪሳራ አጋጥሟል።
ባለፈው ዓመት ለኪሎ 54 ብር ይሸጥ የነበረው የጥጥ ምርት በዚህ ዓመት ወደ 20 ብር መውረዱን ነው በማሳያነት ያነሱት። በገበያ ማጣት ምክንያት እስከ 9 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ሊያጋጥማቸው እንደሚችልም ገልጸዋል።
መንግሥት በእርሻ ወቅት አርሶ አደሮች ገበያ ተኮር ሰብሎች ላይ እንዲያተኩር በሰጠው ትኩረት መጠን በምርት ወቅትም ገበያ በማፈላለግ በኩል የሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
አሁን ያጋጠመው የገበያ ችግር በቀጣይ የምርት ዘመን አርሶ አደሮች ዋስትና አግኝተው እንዳያመርቱ ትልቅ ስጋት መፍጠሩን ገልጸዋል።
የገንዳውኃ ጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አስቻለው እስከዚያ እንዳሉት በገንዘብ ችግር ምክንያት አርሶ አደሮች ያመረቱትን ጥጥ ገዝቶና ዳምጦ ለጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ማቅረብ አልተቻለም። ፋብሪካውም ለአካባቢው ኢንቨስተሮችና ነጋዴዎች ማሽነሪውን እያከራየ ለመጠቀም መገደዱን ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የሰብል ግብይት ቡድን መሪ ብርሃኑ አዲሱ ‘የገንዘብ ችግር አጋጥሞናል’ በሚል ምክንያት የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችና ጥጥ መዳመጫዎች ቀጥታ ወደ ግዥ አለመግባታቸው ለዋጋ መቀነሱ በምክንያትነት አንስተዋል።
አርሶ አደሮች የጥጥ ዘር በከፍተኛ ዋጋ ገዝቶ የጥጥ ምርቱን በዝቅተኛ ዋጋ መሸጡ አጠቃላይ በሀገሪቱ የጨርቃጨርቅ ኢንዳስትሪ ላይ ጭምር ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ነው ያነሱት። የመንግስት ተኩረት እንደሚሻም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአፋር ክልል እየተሰበሰበ ከሚገኘው የቆላ መስኖ ስንዴ 675 ሺህ ኩንታል ምርት ይጠበቃል።
Next articleየአማራና የአፋር ክልሎች በሚዲያ አገልግሎት የሚያደርጉትን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግና ለሀገራዊ አንድነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።