
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 7ኛ ዓመት 4ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን ትናንት አካሂዷል፡፡
ምክር ቤቱ በማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች የ2012 በጀት ዓመት ዕቅድን እና ልዩ ልዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቅቋል፡፡
የብሔረሰብ አስተዳድሩ ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ የ2012 በጀት ዓመት የማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ዕቅድ እንደገና ራሱን ችሎ እንዲታይ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር፡፡ በውሳኔው መሠረትም ትናንት ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ለአንድ ቀን የቆየ አስቸኳይ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡
በምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች የግብርና፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ የእንስሳት ሀብት ልማት፣ የምግብ ዋስትና፣ የሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከል እና የሌሎች መሰል ጉዳዮችን ዕቅድ ገምግሞ አጽድቋል፡፡ የብሔረሰብ አስተዳድሩን ያለፉት አራት ወራት የሥራ እንቅስቃሴ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት ቀርቦ ምክር ቤቱ ተወያይቶበታል፡፡ በዝናብ አጠር አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በጥምረት ሊሠራ እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ከማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበው የበጀት ዓመቱ ዕቅድ እና ያለፉት ጊዜያት አፈጻጸም አንፃር በትምህርት ዘርፍ የተሻሉ የተባሉ ተግባራት ተነስተዋል፡፡ በተለይም የዳስ መማሪያ ክፍሎችን ደረጃቸውን ወደ ጠበቁ መማሪያ ክፍሎች ለመቀየር የተደረገው ጥረት አበረታች ነበር ተብሏል፡፡ ቀሪዎቹን የዳስ ክፍሎች ደረጃቸውን ወደ ጠበቁ መማሪያ ክፍሎች ለመቀየር በትኩረት መሠራት እንዳለበት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡
የ2012 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን ምክር ቤቱ እንደ መልካም አፈፃፀም ተመልክቷል፡፡ ባለፈው የትምህርት ዘመን ተምረው እና መዝገብ ተዘጋጅቶላቸው የነበሩ በርካታ ተማሪዎች በዘንድሮው የትምህርት ዘመን አለመገኘታቸው ትልቅ ክፍተት በመሆኑ ከተጠያቂነት ጋር ተያይዞ እንዲመረመር አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በብሔረሰብ አስተዳድሩ መመዝገብ ከነበረበት ተማሪ ውስጥ 82 በመቶ ገደማ ብቻ እንደተመዘገበም ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ትምህርቱን ከቴክኖሎጂ ጋር አስተሳስሮ ለመስጠት የሚደረገው ጥረት በስልጠና እና የሰው ኃይል በማሟላት በትኩረት መሠራት አለበትም ተብሏል፡፡
የጤና ጥበቃ መምሪያ እና የዋግ ልማት ማኅበር የበጀት ዓመቱ ዕቅድ እና ያለፉ ጊዜያት እንቅስቃሴ ታይቶ የአፈፃፀም አቅጣጫዎች ተቀምጦላቸው በምክር ቤቱ ጸድቀዋል፡፡
በመጨረሻም አስፈፃሚው አካል ለብሔረሰብ አስተዳደሩ የተለያዩ ተቋማት ሹመቶችን አቅርቦ አጽድቋል፡፡ በዚህም መሠረት አቶ ተስፋዬ ገብሬ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ እና የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ፣ አቶ ገብረ ሕይወት አዱኛ የብሔረሰብ አስተዳድሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ፣ አቶ ሰይድ ሙሐመድ የብሔረሰብ አስተዳድሩ ቴክኒክ፣ ሙያና ኢንተርፕራይዞች መምሪያ ኃላፊ እና አቶ ሙሉቀን ሞላ የብሔረሰብ አስተዳድሩ ስፖርት መምሪያ ኃላፊ እንዲሆኑ የቀረበውን ሹመት አጽድቋል፡፡ የሚቀጥለው መደበኛ ጉባኤ እስኪካሄድ ድረስም በሌሎች ክፍት ቦታዎች ላይ አስፈፃሚ አካሉ ሹመቶችን እንዲሰጥ ውክልና ሰጥቶ አስቸኳይ ጉባኤው ተጠናቅቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው ከሰቆጣ