በአፋር ክልል እየተሰበሰበ ከሚገኘው የቆላ መስኖ ስንዴ 675 ሺህ ኩንታል ምርት ይጠበቃል።

144
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአፋር ክልል ሶስት ዞኖች በኩታ ገጠም በመስኖ የለማ የቆላ ስንዴ ምርት እየተሰበሰበ መሆኑን የክልሉ እንስሳት፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ዘንድሮ 15ሺህ ሄክታር መሬት በሶስት የመስኖ ልማት ክላስተሮች በቆላ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኢብራሂም መሐመድ ገልጸዋል።
በክልሉ በአዊሲ ረሱ፣ ገቢ ረሱ እና በሀሪ ረሱ 8ሺህ 557 ሄከታር መሬት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በቆላ ስንዴ መስኖ ማልማት እንደተቻለ አስረድተዋል።
አቶ ኢብራሂም አክለውም በሶስቱም ዞኖች በኩታ ገጠም በመስኖ ለምቶ የደረሰው የስንዴ ሰብል ምርት በአሁኑ ወቅት በኮምባይነር እየተሰበሰበ ይገኛል ብለዋል።
በቆላ መስኖ ስንዴ ልማቱ 43 ባለሃብቶች፣ 170 ከፊል አርብቶ አደሮች እና በማህበራት የተደራጁ 330 ወጣቶች ተሳትፈዋል ብለዋል።
ከቆላ መስኖ ስንዴ ልማቱ 675ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ አቶ ኢብራሂም ገልጸው ለዕቅዱ ሙሉ በሙሉ አለመተግበር የምርት ማሳደጊያ ግብዓት አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ለሚካሄደው የቆላ መስኖ ስንዴ ልማት የምርጥ ዘር እጥረት እንዳያጋጥም በ470 ሄክታር መሬት ላይ ከወረር ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ምርጥ ዘር የማባዛት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በክልሉ አዊሲ ዞን የዱብቲ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወል አብዱ እንዳሉት የቆላ ስንዴን በብዛትና በጥራት አልምተን ከራሳችን አልፈን ለውጭ ገበያ ማቅረብ አለብን የሚል አቋም ተይዞ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በወረዳው በመስኖ የሚለማ ሰፊ ለም መሬት፣ በቂ የውኃ አማራጭና አቅርቦት መኖሩን ገልጸው፤ በልማቱ መሳተፍ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች የወረዳው አስተዳደር ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በመስኖ ልማቱ እየተሳተፉ ካሉት የዓለም ማዕድ አግሮ ግሩፕ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ቤተልሄም ኃይሉ እንዳሉት ማኅበሩ ስንዴን ጨምሮ የተለያየ ሰብል ለማልማት 304 ሄክታር መሬት ተረክቦ ወደ ሥራ ገብቷል።
በየደረጃው የሚገኘው አመራር ድጋፍ ስላልተለያቸው እስካሁን 75 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ አልምተው ሰብሉ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በዚህም 40 ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
አክለውም ቀሪው 200 ሄክታር መሬት በጥጥ ሌላውን ደግሞ በአኩሪ አተር፣ በሰሊጥና በማሾ ለማልማት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ወይዘሮ ቤተልሄም ተናግረዋል።
የአፋር መሬት የሰጡትን የሚያበቅልና በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሉም ተባብሮ ተግቶ በመስራት ከድህነት እንዲወጣም መክረዋል።
ወጣት አባስ ሀሮ በበኩሉ 200 ሄክታር መሬት ተረክቦ እስካሁን 150 ሄክታሩን በስንዴ ማልማቱንና ለ60 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል።
በአካባቢው በዓመት ሶስት ጊዜ የተለያየ ሰብል አልምቶ መጠቀም ይቻላል ያለው ወጣት አባስ፤ ወጣቶች በልማቱ ተሳትፈው በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን ችለው ሌሎችን ተጠቃሚ እንዲያደርጉም መክሯል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleኢትዮጵያ እና ጀርመን የ17 ሚሊዮን ዩሮ የደን እና የደን ውጤቶች ልማት ሥምምነት ተፈራረሙ፡፡
Next articleመንግሥት በጥጥ ምርት የተፈጠረውን የገበያ ችግር እንዲፈታላቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ጠየቁ።