ኢትዮጵያ እና ጀርመን የ17 ሚሊዮን ዩሮ የደን እና የደን ውጤቶች ልማት ሥምምነት ተፈራረሙ፡፡

96
ባሕር ዳር:መጋቢት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ከጀርመን መንግሥት የልማት ባንክ ጋር በደን እና የደን ውጤቶች ልማት የ17 ሚሊዮን ዩሮ ሥምምነት ተፈራረመ፡፡ ሥምምነቱ በደን ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በአካባቢ ብዝሃ ህይዎት ጥበቃ እና የውጭ ምንዛሬን በመቀነስ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ከሦስት ዓመታት በፊት ከጀርመን መንግሥት የልማት ባንክ ጋር የ26 ሚሊዮን ዩሮ የደን ልማት ሥምምነት ተፈራርሞ እየሰራ ቆይቷል ያሉት የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለስልጣን የደን እና ዱር እንስሳት ዘርፍ ምክትል ኅላፊ አቶ ተሾመ አግማስ ናቸው፡፡ ሥምምነቱ በደቡብ ወሎ ዞን ስድስት ፕሮጀክቶች እየተተገበረ ነው ያሉት የዘርፍ ምክትል ኅላፊው ኮሮና እና የጸጥታ ስጋት በነበረባቸው ወቅቶች ከነበረው ዝቅተኛ አፈጻጸም ውጭ አበረታች ውጤቶች አምጥቷል ብለዋል፡፡
በቅርቡ የተደረገው የ17 ሚሊዮን ዩሮ ሥምምነት ካለፈው የቀጠለ እና ሁለተኛ ዙር ነው ያሉት አቶ ተሾመ 13 ሚሊዮን ዩሮ በጀርመን መንግሥት የልማት ባንክ፣ ሦስት ሚሊዮን ዩሮ በክልሉ መንግሥት እና 1 ሚሊዮን ዩሮ በሕዝብ ተሳትፎ የሚሸፈን ነው ተብሏል፡፡ በሥምምነቱ መሰረት 2 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በደን ይለማል ያሉት አቶ ተሾመ የደን ውጤቶች እሴት ልማት እና የሕዝብ ተጠቃሚነት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች በቡድን ተደራጅተው እስከ 1 ነጥብ 5 ሄክታር የወል መሬት ደን ያለማሉ ተብሏል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከማሽነሪ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር የውል ሥምምነት ተወስዶ ወጣቶች በእንጨት እና የእንጨት ውጤቶች ዙሪያ የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል ተብሏል፡፡ እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ ፕሮጀክቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልጸው በደን ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በአካባቢ ብዝሃ ህይዎት ጥበቃ እና የውጭ ምንዛሬን በመቀነስ በኩል ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ክልሉ በደን ልማት ላይ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በትብብር በመስራት የተሻለ እና ለተሞክሮ የሚሆን ልምድ አካብቷል ያሉት አቶ ተሾመ የተሻለ አፈጻጸም እና ለውጥ በማምጣት በአካባቢ ጥበቃ እና የደን ልማት ሥራዎች ላይ ሞዴል መሆን የሚችልበት አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleመከላከያ ሚኒስቴር በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ ለደቡብ ዕዝ የገነባውን የጦር መምሪያ ካምፕ አስመረቀ።
Next articleበአፋር ክልል እየተሰበሰበ ከሚገኘው የቆላ መስኖ ስንዴ 675 ሺህ ኩንታል ምርት ይጠበቃል።