
ባሕር ዳር:መጋቢት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የብልጽግና ፓርቲ አባላት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ውይይት ማካሄድ ጀመሩ።
“የተገኙ ድሎችን ማጽናትና ፈተናዎችን መሻገር” በሚል መሪ ሃሳብ በመካሄድ ላይ ባለው የውይይት መድረክ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ እንድትራመድ ብልጽግና ፓርቲ በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገቡ ተነስቷል።
ኢትዮጵያን ከነበረችበት የኢኮኖሚ ቀውስ በማዳን የዴሞክራሲ ስብራቶች እንዲጠገኑ በማድረግ ረገድ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸው ተገልጿል።
የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ሁሉም ተዋናዮች በእኩልነት እንዲሳተፉ በማድረግ አካታች የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ሂደት እውን መሆኑ ተነስቷል።
የይቅርታና የምህረት ዕሳቤን መፍጠር፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ታስረው የነበሩ ሃይሎችን በመፍታት በነፃነት ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መደረጉም እንዲሁ።
ከሀገር ወጥተው የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎች እንዲገቡ ማድረግ በፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ውስጥ የተመዘገቡ ስኬቶች መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡

አሳሪ የነበሩ ሕጎችን መለወጥና ማሻሻል፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ነጻነትና አቅማቸውን ማጠናከርም በፖለቲካው ዘርፍ ከተመዘገቡት ውጤታማ ሥራዎች መካከል ሆነው በመድረኩ ተጠቅሰዋል።
በለውጡ ዓመታት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከነበረበት ውድቀት በማንሳት እንዲሁም የውጪ ዕዳን የማቃለል እና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመተግበሩ የተገኘው ተጨባጭ ውጤት ተነስቷል።
ሀገራዊ ልማትንና ዕድገትን ከማስቀጠል አንፃር የአረንጓዴ አሻራ፣ የህዳሴ ግድብን ከነበረበት ችግር በማውጣት ግንባታውን አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ማድረስ መቻሉ ተመላክቷል።
ኢትዮጵያን ከስንዴ ተመጽዋችነት ወጥታ ምርት ወደ ውጪ ሀገር መላክ የጀመረችበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑም ተገልጿል።
የማኅበራዊ ትስስርን ማጠናከርና የዜጎችን ክብር የማከም ሥራም ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከተከናወኑ ዐበይት ስኬቶች መካካል ተጠቃሽ ሆነዋል።
በለውጡ ሂደት የገጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶችን በማንሳት በቀጣይም ችግሮችን በጋራ የመፍታት ሥራ ይቀጥላል ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!