
በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የጤናው ሴክተር ብቻ ወደ 14 ቢሊዮን ብር ጉዳት ደርሶበታል
ባሕር ዳር :መጋቢት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ጦርነት በነበረባቸው ቀጠናዎች የሚኖሩ 40 በመቶ የሚኾኑ እናቶች በቤት ውስጥ እንደሚወልዱ የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ጋሹ ክንዱ (ዶ.ር) ገልጸዋል። ይህንን ያሉት በሰሜን ወሎ ዞን በጦርነት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ በመገንባት የእናቶች እና ህጻናት ጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ያለመ ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ በተደረገበት መድረክ ላይ ነው።
ይህ ፕሮጀክት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር በመኾን የሚፈጸም ነው። ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር ሲገባ የወደሙ ተቋማት ይገነባሉ፣ የህክምና ቁሳቁሶች ይሟላሉ እንዲሁም የባለሙያዎችን አቅም በስልጠና ያሻሽላል ተብሏል።ፕሮጀክቱ በዞኑ እናቶች እና ህጻናት ጤና መሻሻል ላይ በትኩረት እንደሚሠራም ተጠቁሟል።
ዶክተር ጋሹ በአማራ ክልል በጦርነት ምክንያት የጤናው ሴክተር ብቻ ወደ 14 ቢሊዮን ብር ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል። ከዚህ ውስጥ ከ51 በመቶው በላይ በሕክምና ቁሳቁሶች ላይ የደረሰ ውድመት ነው። 118 አምቡላንሶች እንደተዘረፉ እና አሁን ላይ ምንም አምቡላንስ የሌላቸው ወረዳዎች ስለመኖራቸውም ተመላክቷል።
በሰሜን ወሎ ዞን ተግባራዊ የሚኾነው የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት የደረሱ ጉዳቶችን መልሶ በመገንባት እናቶች በጤና ጣቢያ እንዲወልዱ እና ማኅበረሰቡም ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ዶክተር ጋሹ በተለይም የተዘረፉ ውድ የሕክምና ቁሳቁሶች እንዲተኩ ሰፊ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል። የወደሙ የጤና ተቋማትን ሙሉ በሙሉ መልሶ በማደራጀት የክልሉን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል አጋር አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። የጤና ባለሙያዎች እና ማኅበረሰቡም የበኩሉን ርብርብ በማድረግ የጤና ተቋማትን አቅም መልሶ መገንባት መቻል አለበት ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!