የጣናን እና የህዳሴ ግድብን አካባቢ የሥነ ምሕዳር ችግሮች ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልግ የዓባይ ተፋሰስ አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

74
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዓባይ ተፋሰስ አሥተዳደር የህዳሴ ግድብ፣ የጣና አካባቢ ሥነ ምሕዳር እና የውኃ ሃብት አሥተዳደር ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።
የዓባይ ተፋሰስ አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የወንድወሰን መንግሥቱ፤ የሕዳሴ ግድብ እና የጣና ሐይቅ አካባቢ ሥነ ምሕዳር ችግሮችን መቅረፍ ተገቢ መኾኑን ተናግረዋል።
ኀላፊው ከፍተኛ ሀገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ጠቀሜታ ያለው የዓባይ ተፋሰስ፤ ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ሥፋት 20 በመቶ እንደሚሸፍንም አስረድተዋል። ከ30 በመቶ በላይ የሀገሪቱ ነዋሪዎች በተፋሰሱ አካባቢ ይኖራሉ ያሉት አቶ የወንድወሰን፤ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የገጸ ምድር የውኃ ሃብትም 45 በመቶ የሚገኘው ከዓባይ ተፋሰስ መኾኑንም አስረድተዋል።
የተፋሰሱ አካባቢ ካለው ጠቅላላ ስፋት 60 በመቶው ለእርሻ ምቹ እንደኾነም አስገንዝበዋል። ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለመስኖ እና ለመኸር እርሻ ምቹ መኾኑን ጠቁመዋል። ተፋሰሱ ከፍተኛ የእንስሳት እና የአሳ ሃብት የሚገኝበት፣ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች የሚገኙበት ቢኾንም በርካታ ችግሮች የተጋረጡበት አካባቢ መኾኑንም ጠቁመዋል።
በተፋሰሱ ዙሪያ የተፈጥሮ ሃብት መመናመን ፣ የጎርፍ መከሰት፣ የጣና ሐይቅ በመጤ አረም መወረር ዋና ዋናዎቹ የተፋሰሱ ችግሮች ናቸው ነው ያሉት። እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት ሀገራዊ ችግሮችን መፍታት በመኾኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ውይይቱ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እና የአካባቢውን መጻኢ እድል ለመወሰን የሚያስችሉ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበት እና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚጠቆሙበት ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
May be an image of 6 people, people sitting and people standing
የብሔር ብሔረሰቦች አሻራ ያረፈበት የህዳሴ ግድብ፤ የዚህ ተፋሰስ አንዱ አካል መኾኑ ጉዳዩ ከፍ ያለ ትኩረት እንደሚገባው አመላካች እንደኾነም ነው ያስረዱት።
የህዳሴ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ እና ቀጣይ ሌሎች ችግሮች እንዳያጋጥሙት ችግሮችን መርምሮ መሥራትም ከሁሉ የሚጠበቅ ጉዳይ መኾኑ ተገልጿል። የጣና ሐይቅን መጠበቅ የሕዳሴ ግድቡን መጠበቅ በመኾኑ ጣናን ከተጋረጠበት ችግር ማውጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ የውኃ እና ኢነርጅ ሚኒስቴር የውኃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ.ር) በበኩላቸው ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ቀድሞ ከነበረው አስተሳሰብ ወጥቶ ጉዳዩን የሚመጥን ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል። ነገር ግን በርካታ ሰዎች በውኃ ችግር ሲሰቃዩ ጥቂቶች በጎርፍ የሚበሉበት አጋጣሚ መኖሩንም ነው የተናገሩት። የውኃ ሃብትን መጠበቅ ለአንድ አካል የተተወ ሳይኾን ኹሉም የሚሳተፍበት ለማድረግ እየተሠራ ስለመኾኑም አስረድተዋል።
ህዳሴ ግድብ ከኀይል ማመንጨት በተጨማሪ ሌሎች የኢኮኖሚ አማራጮችን ለሀገሪቱ እንዲያበረክት የውኃ ሃብትን መንከባከብ ተገቢ ነው ብለዋል። ህዳሴ ግድብ ላይ ችግሮች እንዳያጋጥሙ የውኃ አካላትን መንከባከብ ተገቢ መኾኑንም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሚደረጉ ጥናቶችን ወደ ተግባር በመለወጥ እና አካባቢን የሚጠብቁ ሰዎችን ከጉዳት መከላከል ቅድሚያ የሚሠጠው ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረው ጉዞ ማሳያዎች ናቸው።
Next article“በአማራ ክልል ጦርነት በነበረባቸው ቀጠናዎች 40 በመቶ እናቶች በቤት ውስጥ እየወለዱ ነው” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ