
ዘንድሮ ከበጋ መስኖ 52 ሚሊዮን ኩንታል ምርትም ይጠበቃል።
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአረንጓዴ አሻራ፣ ስንዴ ልማትና በሌማት ትሩፋት የተመዘገቡ የግብርና ዘርፍ ስኬቶች ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረው ጉዞ ማሳያዎች መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የጀመረችው የስንዴ ልማት ፍሬ አፍርቶ ከውጭ የሚገባውን ከማስቀረት ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ጀምሯል።
ከለውጡ ማግስት በሶስት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው የበጋ መስኖ ልማት በየዓመቱ እየጨመረ መጥቶ ዘንድሮ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል፤ ከዚህም 52 ሚሊዮን ኩንታል ምርትም ይጠበቃል።
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉ ቆይታ፤ ግብርናው የኢትዮጵያን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የተሰጠውን ተልዕኮ እያሳካ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በስጋና እንቁላል፣ ዶሮ፣ ማር፣ ወተትና አሳ ሀብት ልማት ከ26 ሺህ በላይ መንደሮችን በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በስንዴ፣ በበቆሎና ጤፍ ምርት ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ዘርፉ የተሰጠውን ተልዕኮ ማሳካት የሚያስችል ተጨባጭ ለውጥ መታየቱን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በ2013 በጀት ዓመት የግብርናው አገራዊ ምርት 5 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም በ2014 በጀት 6 ነጥብ 1 በመቶ ጥቅል እድገት በማስመዝገብ ተስፋ ሰጭ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
በለውጡ ዓመታት ግብርናውን ለማሳደግ ከታዩ አዳዲስ ጅማሮዎች መካከል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 20 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ 26 ቢሊዮን ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የተተከሉ ችግኞች የፍራፍሬና የደን ልማት ጭምር በመሆናቸው ለግብርናው ምርትና ምርታማነት የጎላ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል፡፡
በተያዘው የምርት ዘመን የግብርናው ዘርፍ የተሻለ ዕድገት ለማስመዝገብ አላማ ተይዞ መሰራቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የወጭ ንግድን ማስፋትና ገቢ ምርቶችን መተካት የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የሚያስችል ምርት ለማምረት የቴክኖሎጂ አቅርቦት ሜካናዜሽንና የግብርና ግብዓት በስፋት እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ በአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መናር እንዳይቸገር ባለፈው ዓመት 15 ቢሊዮን ብር ፤ዘንድሮ ደግሞ 21 ቢሊዮን ብር ለማዳበሪያ ግዢ ድጎማ ተደርጓል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!