የጎርጎራ ፕሮጀክት በአራት ወራት ውስጥ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።

132
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ አገር ቱሪዝምን ለማስፋፋት በመላ ሀገሪቷ ስምንት የ«ገበታ ለትውልድ» አዳዲስ ፕሮጀክቶች ሊጀመሩ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል፡፡
በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንደገለጹት፤ የቱሪዝሙን ዘርፍ ለማስፋፋት እንደ አገር እየተከተልነው ያለውን መንገድ የምክር ቤት አባላት ሊደግፉ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ሊሸጥ የሚችል ታሪክ፣ መልክዓምድርና ባህል ቢኖርም የትራንስፖርት፤ የማረፊያና መዝናኛ ስፍራዎች ባለመዘጋጀታቸው ከቱሪዝም መጠቀም ያለብንን ያህል እየተጠቀምን አይደለም ብለዋል፡፡
‹‹ገበታ ለትውልድ›› ከወር በፊት መጀመሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለግንባታው እስከ ሰባት ቢሊዮን ብር ለማግኘት አቅደናል ብለዋል፡፡ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜም ከሕዝቡ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ገንዘብ ስድስት የ‹‹ገበታ ለትውልድ›› እና ሁለት በግል የሚሠሩ በድምሩ ስምንት ፕሮጀክቶችን ለመሥራት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ ከሚሠሩት ፕሮጀክቶች ውስጥ በትግራይ ክልል በገራዓልታ አካባ የሚከናወነው አንዱ ሲሆን፣ አሁን የጀመርነው የሰላም ሂደትም ለግንባታው መፋጠን ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
May be an image of body of water
ፕሮጀክቶቹ ከትግራይ በተጨማሪ በአማራ ክልል ሐይቅ፣ በኦሮሚያ ክልል በጅማ፣ በአፋር ክልል፣ በደቡብ ክልል አርባምንጭ፣ በሱማሌ ክልል እንደሚገኙ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ከፋሲካና ከረመዳን ጾም በኋላ ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በግል ከሚሠሩት ፕሮጀክቶች መካከል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህዳሴ ግድብ አካባቢና ሚዛን አካባቢ የሚሠሩ ፕሮጀክቶቸ እንዳሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለእነዚህም የዲዛይን ሥራ መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡ ስምንቱ ሲሠሩ እየተሠሩ ያሉት የመዝናኛ ቦታዎች ብዛት ከፍ የሚል በመሆኑ ለቱሪዝም እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በዚህ መንገድ ቱሪዝምን እያስፋፋን እንሄዳለን ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም አካባቢ እንዲገነባ ጥያቄዎች አሉ፤ ነገር ግን የተጀመሩት ሊጠናቀቁ ይገባል፤ በጥቅሉ ቱሪዝም አካባቢ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች አሉ ብለዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ለቱሪዝም እድገቱ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በ ‹‹ገበታ ለሸገር›› ፕሮጀክት አዲስ አበባ ውስጥ ታሪካዊ ሥራ መሥራት ተችሏል፡፡ አዲስ አበባን እንደ ስሟ እናደርጋታለን ብለን ስንጀምር ብዙ ፈተና ይገጥሙናል ብለን ባናስብም እየሠራንና እየገነባን ስንሄድ ሊሠሩ የሚገባቸው ብዙ ሥራዎች እንዳሉ ተገንዝበናል፡፡ ወደፊትም በስፋት እንሄድበታለን ብለዋል፡፡
ከአዲስ አበባ አልፈን ኢትዮጵያን ለማዳረስ ባደረግነው ጥረት ‹‹ገበታ ለሀገር›› የጎርጎራ ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጎርጎራ አራት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስ ጥ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ሲሉም ተናግረዋል ፡፡
ኢፕድ እንደዘገበው፤ የጎርጎራ ፕሮጀክት በአፍሪካ ከአንድ እስከ ሦስት ምርጥ ቦታዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ለታሪክና ለትውልድ የሚተላለፍ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ወንጪ፣ አላላ ኬላና ኮይሻ ላይ የተሠሩ ሥራዎች በጥራታቸውና በጊዜያቸው ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ አሁንም ውስን በመሆናቸው እየተስፋፉ መሄድ አለባቸው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አብራርተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአማራ ክልል ከ“የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከ880 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ እየተሠራ ነው።
Next articleበግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረው ጉዞ ማሳያዎች ናቸው።