የአማራ ክልል ባለው የማዕድን ሀብት ልክ ተጠቃሚ አለመሆኑ ተገለጸ፡፡

915

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ከሚገኝባቸዉ አካባቢዎች መካከል የአማራ ክልል ተጠቃሽ ነው፡፡ በክልሉ በወሎ አካባቢ ለተለያዩ ጌታጌጥ ሥራዎች የሚውሉ እንደ ኦፓል ዓይነት ማዕድናት በብዛት ይገኛሉ፤ የዓባይ ሸለቆን እና በሰሜን ሸዋ ዞን የጀማ ተፋሰስን ተከትሎ ደግሞ ለኢንዳስትሪ ግብዓት እና ለተለያዩ ተግባራት የሚውሉ በርካታ የማዕድን ሀብቶች መኖራቸውን የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል፡፡

‹‹ምንም እንኳ በክልሉ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ቢኖርም ከዕውቀት እና ክህሎት እጥረት እንዲሁም ከትኩረት ማነስ በመነጨ ምክንያት ክልሉ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም አላገኘም›› ብለዋል የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዘውዱ ለገሰ፡፡

በክልሉ ብቻ ሳይሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊያሠራ የሚችል ግልጽና አስተማማኝ ፖሊሲ እና ስትራቴጅ ባለመኖሩ የግል ባለሀብቱ በልማቱ እንዳይሳተፍ ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ ሆኖ መቆየቱንም ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡

ጥራት ያለው እና በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥነ ምኅዳራዊ መረጃ በማዘጋጀት በክልሉ ያለውን የማዕድን ሀብት መገኛ እና ዓይነት በመለዬት ዘርፉን ማሳደግ እና የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ማሳደግ እና የኢንዱስትሪ ግብቶችን ማቅረብ እንደሚያስፈልግም አቶ ዘውዱ አመልክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ

Previous articleየደረሱ ሰብሎች በዝናብ ጉዳት ሳይደርስባቸው ቀድሞ መሰብሰብ እንደሚገባ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡
Next articleበአማራ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይሄዱ በትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ የተነገራቸውና የቀሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ገለጹ፡፡