
የሚገኘው ገቢ ለፋሲል ግንብ ጥገና፣ ማስዋቢያና ማልሚያ የሚውል ነው
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከ“የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ የመጀመሪያ ዙር ሽያጭ እና በአንድ ወር ውስጥ ከሚከናወኑ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች ከ880 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) 10 ሺህ በአማርኛ 1 ሺህ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች የታተሙ 11 ሺህ መጽሐፍት ደርሶናል ብለዋል፡፡ በዙር እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
ሁሉም በሽያጭ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መጽሐፉን ለሽያጭ ከማቅረብ ባሻገር በጥቅሙና ፋይዳው ላይ ተመስርቶ እንዲሸጥ፣ እንዲተዋወቅ እና የተሻለ ገቢ እንዲያስገኝ እንዲሁም በየደረጃው ለሚገኘው ማሕበረሰብ የአስተሳሰብ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ስላለው ለሐሳብ መገንቢያ እንዲውል ይሠራል ብለዋል፡፡
መጽሐፉ ለልማት አንድ አቅም እንዲሆን በክልሉ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች እንዲካሄዱ መታቀዱን እና በዚህም ባለሃብቶች፣ ተቋማት፣ ታዋቂ ሰዎች እና የተለያ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ነው ያሉት፡፡
ገቢው ለፋሲል ግንብ ጥገና፣ ማስዋቢያ፣ ማልሚያ እንደሚውል ጠቁመው ለዚህ በጎ ዓላማ የክልሉ ሕዝብ በመጽሐፉ ግዥ እና በገቢ ማሰባሰቢያዎቹ በንቃት እንዲሳተፍ ጠይቀዋል፡፡

ከ11 ሺህ መጽሐፍት ቀጥታ ሽያጭ 4 ሚሊየን 950 ሺህ አንዲሁም ከገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች 875 ሚሊየን በአጠቃላይ ከ880 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን 1 መጽሐፍ 500 ሺህ ብር የገዛ ተቋም መኖሩንም አመላክተዋል፡፡
የገንዘብ አሰባሰቡን ሂደት ሥርዓት ለማስያዝ የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ የሚከታተለው የጋራ ገቢ ማሰባሰቢያ የባንክ ሂሳብ ቁጥር መከፈቱን አረጋግጠዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የሚመሩት ኮሚቴ ዕቅዱን ለማከናወን ክልላዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ ለአስፈጻሚ አካላት አቅጣጫ መስጠቱን አብራርተዋል፡፡
ከመጋቢት 14 ጀምሮ ሥራው እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ለአንድ ወር እደሚቆይም አስረድተዋል፡፡
ለግንባታ ሥራው ሁለት ጥናቶች መጠናታቸውን ጠቁመው፤ ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄደው የመጀመሪያው ጥናት ውጤት በወጪ ደረጃ እስከ 500 ሚሊየን ብር በጊዜ ረገድ ከ1 ዓመት ተኩል እስከ 2 ዓመት ይወስዳል የሚል ነው ብለዋል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የተጠናው ሁለተኛው የጥናት ውጤት ደግሞ እስከ 745 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግ እና ከ1 ዓመት እስከ 1ዓመት ከ8 ወር ባለው ጊዜ እንደሚጠናቀቅ አመላክቷል ነው ያሉት፡፡
የሚቀድመው ገንዘብ ማሰባሰቡ መሆኑን ገልጸው ጥናቶቹ ከተጠኑ ስለቆዩ እና የዋጋ ሁኔታው እየጨመረ ስለሆነ እንደሁኔታው ጥናቱ ሊሻሻል እንደሚችልም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!