
ባሕርዳር: መጋቢት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሃራ በርሃ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርገውን መስፋፋት መካች ዘቦች ተደርገው ከሚወሰዱት የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎች ውስጥ አንዱ ነው የጎደቤ ፓርክ፡፡
ፓርኩ በዞኑ ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ጎደቤ በተባለው ስፍራ ይገኛል። ከ18 ሺህ 600 በላይ ሄክታር መሬት ይሸፍናል፡፡ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ መንግሥት በጥብቅ ደንነት ተከልሎ ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በብሔራዊ ፓርክነት ተመዝግቧል፡፡ በውስጡ ከ27 በላይ የዱር እንስሳት፣ ከ57 በላይ የተለያዩ የአዕዋፍ ዝርያዎች፣ ከ81 በላይ የዕፅዋት ዓይነቶች መገኛም እንደኾነ የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት የሥነ ምህዳር ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ ይርጋ ታከለ ነግረውናል፡፡
ጎደቤ ፓርክ በሄክታር እስከ 76 ቶን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ የማመቅ አቅም አለው ተብሏል፡፡ ወደ ካርቦን ገበያ መግባት ቢቻል ደግሞ ፓርኩ ሲከለል በነበረው የደን ሽፋን እንኳ በዓመት ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዶላር ገቢ ማስገኘት እንደሚችል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናት መደረጉን ባለሙያው ነግረውናል። አሁን ላይ የደን ሽፋኑ በመጨመሩ ሽያጩ እንደሚጨምር ባለሙያው ገልጸዋል።
በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ “አረንጓዴ ዘብ” እየተባሉ ከሚጠሩት ሌሎች ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎች ውስጥ በምዕራብ ጎንደር ዞን ከሚገኙት አልጣሽ፣ ማኅበረ ሥላሴ፣ ሽመለጋራ፣ ጎደቤ፣ የአንገረብ እና የቃፍታ ሁመራ ፓርኮችና ማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራዎች ተጠቃሾች ናቸው።
እነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የሳር፣ ቁጥቋጦ እና የዕጽዋት ሽፋን ያላቸው በመሆኑ በክረምት ወቅት የአካባቢውን ሙቅት በመቀነስ አስተዋጽኦዋቸው የጎላ ነው።
ከደጋማው የሀገሪቱ ክፍል ተነስተው ወደ ቆላማው ክፍል የሚወርዱ ወንዞችን ውኃ በስፋት ስለሚጠቀሙ ለደን ሽፋኑ መስፋፋት እንደ አንድ ምክንያት ተቀምጧል። ከሱዳን ፀሐያማ ወቅት የሚመጣውን አስቸጋሪ አሸዋማ ነፋስ የመከላከል አቅምም አላቸው።

የሰሃራ በርሃ ከሰሜን አፍሪካ ተነስቶ ወደ ደቡብ እና ምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ደግሞ ምዕራብ ሱዳንን ሲያጠቃ በዓመት በ100 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ይስፋፋ እንደነበር ይነገራል፡፡ እነዚህ ደኖች የበርሃማነቱን መስፋፋት ፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርገውን ጉዞ ወደ 10 ኪሎ ሜትር ዝቅ እንዲል አድርገዋል።
ደኖቹ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን በማመቅ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡
ደኖች ካርቦንን ከማመቅ ባለፈ የበርሃማነት መስፋፋትን በመከላከል፣ የሥነ ምህዳር ውኃ የመያዝ አቅምን በማጎልበት፣ የመሬት መሸርሸርን በመከላከል፣ የዝናብን የተፈጥሮ ኡደት ለማስቀጠል ጥቅማቸው የጎላ ነው።
የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሠረት ብርሃኑ በፓርኩ የሕገወጥ እርሻ፣ የሰደድ እሳትና የልቅ ግጦሽ ችግሮች ሲከሰቱ ፈጥኖ ለመከላከል የመንገድ ችግር መኖሩን ገልጸዋል።
በማኅበረሰቡ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ለአካባቢው ማኅበረሰብ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ከዚህ አልፈው ሕግ ተላልፈው በተገኙ ግለሰቦች ደግሞ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑን ነው የነገሩን። መንግሥትም ለፓርኩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ፓርኩን ለመጎብኘት ለሚፈልግ፦
. ከባሕር ዳር 411 ኪሎ ሜትር
. ከጎንደር ደግሞ 237 ኪሎ ሜትር እንዲሁም
. ከወረዳው ዋና ከተማ አብርሃጅራ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!