
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የረመዷን ወር የእስልምና ሀይማኖት ከተገነባባቸው አምስት መሰረቶች አንዱ የሆነው ጾም የሚከወንበትና በሂጅራ አቆጣጠር ከ12ቱ ወራቶች 9ኛው ወር ነው፡፡
የረመዷን ወር ፈጣሪ የሙስሊሞች የሕይወታቸው መመሪያ የሆነውን ቅዱስ ቁርኣን በጅብሪል አማካኝነት ለነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ያወረደበት የተቀደሰ ወር ነው፡፡
በረመዷን ወር አሏህ (ሱ.ወ.) በባሮቹ ላይ ጾምን ግዴታ አድርጐ ደንግጓል (አል – በቀራህ ፡183)
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፡- “በወረሃ ረመዷን የገነት በሮች ይከፈታሉ፣ የገሀነም በሮች ይዘጋሉ፡፡ ሰይጣናት ይታሰራሉ” ብለዋል፡፡ (በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ) በረመዷን ዋዜማ የመልካምነቱ ዝና መሰማት ይጀምራል፡፡ ሰላም ይሰፍናል፡፡ የተጣሉ ይቅር ለፈጣሪ ይባባላሉ፡፡ አማኞች ራሳቸውን እያዩ ከፈጣሪ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያስተካክሉበት ወር ነው፡፡
በረመዷን ወር ሕዝበ ሙስሊሙ ጐህ ከቀደደበት ጀምሮ ጀምበር እስክትጠልቅበት ጊዜ ድረስ ራሱን ከምግብ፣ ከመጠጥና ከወሲብ አግዶ መያዝ እንዲሁም ከመጥፎ ንግግር እና ከሀሜት በመቆጠብ ፈጣሪን ብቻ በማስታወስ የፈጣሪውን ትእዛዝ የሚተገብርበት መለኮታዊ ወር ተደርጐ ይወሰዳል፡፡
ከሕመምተኞች፣ በጉዞ ላይ ካሉ፣ በወር አበባ ላይ ከሚገኙ ሴቶችና ለአቅመ አዳም/ሄዋን ያልደረሱ ሕፃናት በስተቀር ሁሉም ሙስሊም ረመዷንን መጾም ግዴታው ነው፡፡
የእዝነት፣ የምህረት እና በአላህ ፈቃድ ከእሳት ነፃ የሚሆኑበት ወር እንደሆነ የሚታመነው የረመዷን ወር በመልካምነት የተሞላ ነው፡፡
በዚህ ወር ውስጥ የሚሠሩ በጐ ሥራ ከሌሎች ጊዜያቶች ከሚሠራ መልካም ተግባር ሁሉ እጥፍ ድርብ ነው፡፡
የረመዷን ጾም የሰው ልጆች በሕይወታቸው ውስጥ በተለያዩ ባህሪያቶችና ተግባራቶች፣ ያሳለፏቸው እና ያጠፏቸው ጥፋቶች በንሰሀ ለማካካስና ለማስተካከል የሚሰጥ እድል ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡
የረመዷን ጾም ለሰው ልጅ ለነፍስያው ትዕግሥት ማለማመድ፣ ስጋዊ ፍላጐቶችን መርታት ይቻል ዘንድ የመንፈስ ጥንካሬን ያጐለብታል፡፡
በረመዷን የሰው ልጅ በጐ ሥራን እንዲለማመድ ለድሆች እና ለችግረኞች እንዲያዝን እና እንዲያስብ ይሆናል፡፡ ይህም አንድ ሰው በጾም ወቅት ሲራብና የረሃብን ምንነት በተግባር ሲረዳ ልቡ ለድሆች እንዲያዝንና ችግራቸው እንዲሰማው በማድረግ ነው፡፡
ሌላው የረመዷን ትሩፋት በማፍጠሪያ ሰዓት ከቤተሰብ እና ከወዳጆች ጋር ተሰባስቦ አብሮ መብላት መጠጣት፤ በረመዷን ወር ብቻ የሚገኘውን የተራዊህ ስግደት ዘር፣ ቀለም፣ ቋንቋ ፣… ሳይለይ በመስጅድ ውስጥ ለሰዓታት በአንድነት፣ በኅብረት የሚሰገደው ሰላት ራሱን የቻለ የማኅበራዊ በጐ እሴት ነው፡፡
በአጠቃላይ ሙስሊም ምዕመናን ራሳቸውን የሚያንፁበት፣ ወደ አምላክ የሚቀርቡበት የእምነት እውቀታቸውን የሚያሳድጉበት ልዩ የፆም ወር ነው።
ለእስልምና ዕምነት ተከታዮች እንኳን ለረመዷን ጾም አደረሳችሁ!
በእመቤት አህመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!