በሀገር አቀፍ ደረጃ 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

224
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ግብርና ሚኒስቴር በ2015/16 ዓ.ም የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት ምን መምሰል እንዳለበት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር እየመከረ ነው።
በግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንት እና ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት በአፈር ማዳበሪያ ላይ የተከሰተውን የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመጣጣም ለመቅረፍ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል። በዚህ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽማል። ከተገዛው ውስጥ 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ ላይ ደርሷል ብለዋል። ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ማዕከላዊ መጋዝኖች ላይ ገብቷል ነው ያሉት። የዘር ወቅት ከመድረሱ በፊት ማዳበሪያ በየክልሉ እንደሚገባ ዶክተር ሶፍያ ተናግረዋል።
የአርሶ አደሮችን ፍላጎት ለማሟላት እና ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ ሕገወጥ ነጋዴውን መከላከል ተገቢ መኾኑንም ዶክተር ሶፊያ አንስተዋል።
የቀረበውን ማዳበሪያ በወቅቱ በማሰራጨት እና አርሶ አደሮች የገዙትን የአፈር ማዳበሪያ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።
የማዳበሪያ እጥረቱን ለመቅረፍ አማራጮችን ማየት ተገቢ ነው ያሉት ዶክተር ሶፊያ፤ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያ እያዘጋጁ ነው፣ ይኽም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ፤ 3ቱ የማዳበሪያ ዓይነቶች በተመጣጣኝ ሥብጥር መቅረቡን ተናግረዋል።
በደጋ አካባቢ ቀድመው የሚዘሩ ሰብሎች ላይ በአፈር ማዳበሪያ እጥረት ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የታቀደውን የምርት ጭማሬ ለማምጣት 9 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሠራ ስለመኾኑ ነግረውናል።
ለአማራ ከልል 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል በግብርና ሚኒስቴር የተፈቀደ መኾኑን ጠቁመዋል።
እስካሁንም 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል ወደ ክልሉ የገባ ሲኾን 1ሚሊየን 97 ሺህ 118 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት መጋዝን መግባቱን አረጋግጠዋል።
ወይዘሮ ሙሽራ ከአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪ 199 ሺህ ኩንታል “ሲአንድ” ዘር እና 13 ሺህ ኩንታል “መነሻ” ዘር የተሠበሰበ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት
Next articleረመዷን ታላቅ የለውጥ ወር