
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሶማሌ ክልል ሕዝብ ጽንፈኝነትን በጋራ በመዋጋት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን ማስቀጠል እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ ገለጹ፡፡
የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ፤ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ/ አገዛዝ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የመብት ረገጣ ከተፈፀመባቸው ኢትዮጵያውያን መካከል የሱማሌ ክልል ህዝብ ቀዳሚው ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በአገዛዙ ከፍተኛ በደልና ሰቆቃ እንደደረሰባቸው አስታውሰው ፤ የሶማሌ ክልል ሕዝብም በቀዬው በሰላም ተረጋግቶ እንዳይኖርና የክልሉን ሀብት አልምቶ እንዳይጠቀም ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
ንጹሃንን መጨቆን፣ የሀብት ዘረፋና ምዝበራ፣ አስገድዶ መድፈር፣ እስራትና ግርፋት የስርዓቱ መገለጫዎች ሆነው የሱማሌን ሕዝብ በሀገሩ ባይተዋር እንዲሆን አድርገውት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በተለይም ደግሞ ከለውጡ በፊት የነበሩ አስር ዓመታት ለሶማሌ ክልል ሕዝብ በንብረቱ የማያዝበት፣ ከቤት ወጥቶ በሰላም የማይመለስበት አስከፊ ጊዜ ማሳለፉን ጠቁመዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፣ ከለውጡ በኋላ የሱማሌ ክልል መንግስት ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት፣ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር በውይይት ልዩነቶችን በመፍታት፣ የተፈናቀሉትን በማቋቋም በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ተደርጓል ብለዋል፡፡
በክልሉም ሆነ በፌዴራል ተቋማት ለቁጥር ማሟያ ብቻ ሲደረግ የቆየውን የአመራር ስምሪት በማስቀረት በብቃታቸው ተወዳድረው ኢትዮጵያን ማገልግል የሚችሉ ብቁ አመራሮችን ማፍራት መቻሉንም እንዲሁ።
የሶማሌ ክልል ሕዝብ በአካባቢው በሰፈነው ሰላምና መረጋጋት በተለያዩ የልማት ዘርፎች ተሰማርቶ የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለአብነት የክልሉን ሕዝብ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት ከተገነቡ 18 ሆስፒታሎች መካከል ዘጠኙ የተሰሩት ባለፉት አምስት የለውጥ ዓመታት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ 260 ጥልቅ የከርሰ ምድር ውኃ ጉድጓዶችን በመቆፈር፣ መለስተኛ ግድቦችን በመስራት፣ ስምንት ከተሞችን የውሀ አቅርቦት እንዲኖራቸው በማድረግና ብዙ መንደሮችን የሚያገናኝ የውሃ መስመር ዝርጋታ በማከናወን የክልሉን የውኃ ሽፋን በእጥፍ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ሕዝብ “በንብረቱ የማያዝዝበት፤ ሰብዓዊ መብቱ የሚረገጥበት ዘመን አሁን አክትሟል ያሉት” ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ፤ “በግብርና እና በተለያዩ የልማት ዘርፎች የተመዘገቡ ድሎችን ለማስጠቀል የክልሉን ሰላም በንቃት መጠበቅ እንዳለበት” አሳስበዋል፡፡
ከለውጥ በኋላ በፍትህ አካላት፣ በሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲሁም በዲሞክራሲ ተቋማት ላይ በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገው ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ቋንቋን፣ ሃይማኖትን እና ዘርን ሽፋን ያደረገ የአክራሪነትና የፅንፈኝነት አካሄድ ህዝቡ ታግሎ ያመጣውን ለውጥ እየፈተነ መሆኑን ተናግረዋል።
በጥቂት ቡድኖችና ግለሰቦች አቀንቃኝነት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰላማዊ ዜጎችን እረፍት እየነሳ ያለውን የአክራሪነትና የፅንፈኝነት እኩይ አስተሳሰብና ድርጊት በጋራ መከላከል አለብን ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!