አመልድ ኢትዮጵያ በምስራቅ በለሳ፣ ምዕራብ በለሳ እና እብናት ወረዳዎች የትራኮማ ሥርጭትን ወደ 15 በመቶ ዝቅ ማድረጉ ተገለጸ፡፡

115
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕፃናት፣ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን ኑሮ ማሻሻል ዓላማው ያደረገው የኤንቲዲ-ዋሽ እብናት በለሳ ፕሮጀክት በንጹህ ውኃ መጠጥ ግንባታ፣ የአካባቢና የግል ንጽህና አጠባበቅ እና ትራኮማ ቁጥጥር ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ ቆይቷል ተብሏል፡፡ የፕሮጀክቱ መዝጊያ አውደ ጥናት ዛሬ በባሕር ዳር ሲካሄድ መሰረታዊ ለውጥ አምጥቷል ነው የተባለው፡፡
ከጥር 2015 (እ.አ.አ) እስከ መጋቢት 2023 ላለፉት አምስት ዓመታት በምስራቅ በለሳ፣ ምዕራብ በለሳ እና እብናት ወረዳዎች በአመልድ ኢትዮጵያ ሲተገበር የነበረው የኤንቲዲ-ዋሽ እብናት በለሳ ፕሮጀክት ከ276 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል ተብሏል፡፡ በሦስቱም ወረዳዎች ከአምስት ዓመት በፊት የትራኮማ ስርጭት 60 በመቶ አካባቢ እንደነበር ጥናቶች ያመለክቱ ነበር ያሉት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጊዮን ሹመቴ በአምስት ዓመት ቆይታው ወደ 15 በመቶ እንዲወርድ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ከ36 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የትራኮማ ልየታ ተደርጓል ያሉት አስተባባሪው 4 ሺህ 500 ለሚሆኑ የትራኮማ ተጠቂዎች የቀዶ ጥገና ህክምና ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡ የትራኮማ ስርጭትን በዘላቂነት ለመግታትም ከ414 በላይ የትምህርት ቤት ክበቦች ተቋቁመው ሲሠሩ ቆይተዋል ነው የተባለው፡፡ የትራኮማ ተጠቂዎች በብዛት ሕፃናት ስለሚሆኑ የፊት ንጽሕና አጠባበቅ ባሕል እንዲሆን ሰፊ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት አስተባባሪው፡፡
ፕሮጀክቱ የመጸዳጃ ቤቶች፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማት ግንባታ እና በአቅም ማጎልበቻ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ መቆየቱን ያነሱት አቶ ጊዮን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የጸጥታ ስጋቶች እና የግንባታ ቁሳቁሶች የዋጋ ጭማሪ ፈተናዎች ባሉበት ውጤታማ ሥራዎችን አከናውኗል ነው የተባለው፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ መንግሥት እና ባለሀብቶች በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ተገለጸ።
Next article“የሶማሌ ክልል ሕዝብ ጽንፈኝነትን በጋራ በመዋጋት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን ማስቀጠል አለበት” ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ