
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና የሥራ እድል ፈጠራ የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ትብብር እና ሚና ላይ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት በባሕርዳር ከተማ ተካሄዷል። በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ባየ አለባቸው እየጨመረ የመጣውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት እና ባለሀብቶች በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ለከተማው ወጣቶች የተለያዩ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር ቢሞከርም የሥራ አጦች ቁጥር ግን ሩቅ አሳሳቢ ኾኗል ብለዋል። የሁሉንም ሥራ ፈላጊዎች ፍላጎት ለማሟላት በመንግሥት ጥረት ብቻ የማይቻል በመኾኑ የግል ባለሀብቶችም የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት መወጣት አለባቸው ሲሉ አቶ ባየ ተናግረዋል።
ሥራ ፈላጊዎች የሙያ እና ክህሎት ባለቤት እንዲኾኑ ለማስቻል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በትኩረት መሥራት እንዳለባቸውም ምክትል ከንቲባው አመላክተዋል። ወጣቶች የያዙት ሙያ እና ክህሎት ብቻ ለዳቦ ስለማያበቃ መንግሥት እና ባለሀብቶች በመተባበር ሥራ የሚያገኙበትን እድል መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ፈለቀ ውቤ ወጣቶች የሙያ እና ክህሎት ባለቤት እንዲኾኑ ለማስቻል የተመረጡ ስልጠናዎች በኮሌጁ እንደሚሰጡ ገልጸዋል። ሰልጣኞች የሚጠበቅባቸውን ክህሎት ከያዙ በኋላ የሥራ ትስስር እንደሚፈጠርላቸውም ገልጸዋል።
አቶ ፈለቀ በከተማው የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ከፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ ጋር በመነጋገር ከሰልጣኞች የሚፈልጉትን ክህሎት ማሳወቅ እና አሰልጣኝ መመደብ እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ፋብሪካዎች ሰልጣኞች የተግባር ላይ ልምምድ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እና የምዘና ማዕከል በመኾን ብቃትን ማረጋገጥ መቻል አለባቸውም ብለዋል። የግሉ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች በሙያ የበቁ ወጣቶች በካምፓኒያቸው እንዲቀጠሩ በማድረግ የሥራ አጥነትን ቁጥር መቀነስ እንዳለባቸውም አቶ ፈለቀ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
