ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅን በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ።

96
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅን አስመልክቶ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።
የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረቡት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ፤ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ሁሉን አቀፍ፣ ወጥና አስተማማኝ የሀገሪቷ ነዋሪዎች የሚመዘገቡበት ሥርዓት በመዘርጋት እና የተመዝጋቢዎችን መረጃ በመያዝ የዲጂታል መታወቂያ አጠቃቀም ስርዓትን ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
መታወቂያውን በመጠቀም በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ የግልፅነትና ተጠያቂነት አሠራር ስርዓት እንዲዘረጋና የተሳለጠ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት እንዲኖር አመቺ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።
አዋጁ ረዘም ላለ ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ እፀገነት፤ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት የተጭበረበረ መታወቂያ ሰጥተው ከተገኙ ከበድ ያለ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው እና አስተማማኝነቱም በመርህ ላይ መመስረቱን አስረድተዋል።
ምክር ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1284/2015 አድርጎ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ምዝገባ በሁሉም ትምህርት ቤቶች በበይነ መረብ ብቻ ይካሔዳል”የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን
Next articleየሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ መንግሥት እና ባለሀብቶች በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ተገለጸ።