የአየር ንብረት ለውጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሚያስፈልግበት ደረጃ መድረሱን ተመራማሪዎች አስታወቁ፡፡

145

ከ11 ሺህ በላይ ዓለማቀፍ ተመራማሪዎች ባወጡት ጥናት እንዳመለከቱት ዓለም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስፈልጋታል፡፡
ለ40 ዓመታት የተደረገ ጥናት እንዳመላከተው መንግሥታት ለአየር ንብረት ለውጥ የሰጡት ምላሽ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም የሰው ልጅ የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ፍጹም ተፅዕኖ የከፋ አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡
ተመራማሪዎቹ ከፊት ለፊት እየመጣ ያለውን ሥጋት የመግለጽና የማስጠንቀቅ የሞራል ኃላፊነት እንዳለባቸው በመግለጽ ነው መረጃን ይፋ ያደረጉት፡፡
አዲስ የወጣው መረጃ እንዳመላከተው ያለፈው የአውሮፓውያኑ ጥቅምት ወር በታሪክ ሞቃታማው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ እንደዚህ የሙቀት መጠን እየለኩ መናገር ብቻ የሙቀት መጠኑን እንደማይቀንሰው ያመለከተው ሪፖርቱ በሙቀቱ ምክንያት እየመጣ ያለውን መቅሰፍት ማሰብ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ያለፉትን 40 ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ መረጃዎች ያሰባሰበው ጥናቱ የሰውና እንስሳት ቁጥር መጨመርን፣ የተናጠል የሥጋ ፍጆታን፣ በዓለማቀፍ ደረጃ የደረሰውን የደን ውድመት እና የነዳጅ ፍጆታ ያካተተ ነው፡፡
በእርግጥ ስጋት ብቻ ሳይሆን ተስፋም የታየባቸው ዘርፎች እንዳሉ ተገልጿል፤ የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚነት መሻሻል አንዱ በጎ ጅምር ተብሏል፡፡ በአራት አስርት ዓመታት ውስጥ በየአስር ዓመቱ በ373 በመቶ መጨመሩ ነው ተስፋ ሰጭ ያስባለው፤ ያም ሆኖ ግን ታዳሽ ያልሆነ የኃይል ምንጭ አጠቃቀም በ28 እጥፍ እንደሚበልጥ የ2018 (እ.አ.አ) መረጃ ዋቢ ተደርጎ ተመላክቷል፡፡
ያም ሆኖ ግን የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በአሳሳቢ ሁኔታ እየቀጠለ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚያስፈልገው ተመራማሪዎቹ አሳስበዋል፡፡ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስፈልጋል ስንል የካርቦን ልቀትን፣ የእንስሳት እርባታን፣ የደን ምንጠራንና የነዳጅ ፍጆታን ትርጉም ባለው መንገድ ካልቀነስን በታሪክ ታይቶ ለማይታወቅ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እንጋለጣለን›› ሲሉ ነው ተመራማሪዎቹ ያስጠነቀቁት፡፡ የተወሰኑ የዓለም ክፍሎች የሰው ልጅ ሊኖርባቸው የማይችሉ ሊሆኑ እንደሚችሉም ነው ያመለከቱት፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ
በአብርሃም በዕውቀት

Previous articleእነዚህ ደግ ሕዝቦች በጓሯቸው የልጆቻቸውን ገዳይ እያሳደጉ ነው፡፡
Next articleየደረሱ ሰብሎች በዝናብ ጉዳት ሳይደርስባቸው ቀድሞ መሰብሰብ እንደሚገባ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡