
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጀርመን በርሊን ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የበርሊን “ኢነርጂ ትራንዚሽዝን ዲያሎግ” መድረክ የተገኙት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት የኢነርጂ ሀብት ልማት በመንግሥት ወጪ ብቻ መሸፈን የማይቻል እና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በእጅጉ የሚሻ ነው፡፡
በተለይ እንደ ሀገር ከዋናው የሀይል መስመር ውጭ፤ የሶላር፤ የንፋስና የአነስተኛ ኀይል ማመንጫ አስመልክቶ ጥሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ በዚህ ዘርፍ የግል ባለሀብቶች መሰማራት እ.አ.አ. በ2030 ሁሉንም ዜጎች የኀይል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል፡፡
ሚኒስትሩ በኀይል ዘርፍ ያሉ ተግዳቶችንና መተግበር ያለባቸውን ጉዳዮች አንስተው ሲያብራሩ፤ ኢትዮጵያ ሰፊ የታዳሽ ኀይል የማመነጨት አቅም፤ ከውሃ ፤ ከጸሃይ እና ከነፋስ ኀይል ከፍተኛ ኀይል የማመንጨት አቅም እንዳላት ገልጸዋል::
ነገር ግን አነስተኛ የታሪፍ ተመን፤ የኢነርጂ አማራጮች ቅልቅል (Energy Mix) ላይ የሚታየው ክፍተት እና የተበታተነ የህዝቦች አሰፋፈር ተግዳሮት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለሚመሰማሩ ባለሃብቶች ሊደረግ ስለሚገባው ማበረታቻ ሲያብራሩ፤ የተለያዩ ከታክስ ጋር የተያያዘ የማበረታቻ ሥራዎች እንዲሁም መሬት በነጻ የማቅረብ ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡
በተለይ እንደ ሀገር የተጀመረው በዲዝል የሚሠሩ ለመስኖ የሚያገለግሉ ፓምፖችን ወደ ሶላር ፓምፕ የመቀየር ሂደት ውጤታማ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም የድሪም ፕሮጀክት ጥሩ ማሳ እንደኾነ አውስተዋል፡፡
ከኦፍ ግሪድ ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ለወጣቶች ስልጠና መስጠትና የአነስተኛ እንተርፕራይዞችን አቅም መገንባት ትኩረት እንደሚያስፈልገው ማብራራታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!