በደቡብ ጎንደር ዞን ተቋርጦ የነበረውን የገልዳ ወንዝ የመስኖ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ በ202 ሚሊየን ብር እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

122
ደብረ ታቦር፡ መጋቢት 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ የገልዳ ወንዝ አካባቢ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ግድቡ ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ለአሚኮ ተናግረዋል።
ግንባታው ተደጋጋሚ መሰናክል የገጠመው መኾኑን የገለጹት አርሶ አደሮቹ ሥራው እንዲጠናቀቅ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት ጠይቀዋል፡፡
በገልዳ ወንዝ ላይ በ2008 ዓ.ም ተጀምሮ የነበረው የመስኖ ግድብ ”ቀላል” እና ”የቴክኒክ ችግር” በተባለ ምክንያት ሳይጠናቀቅ ቆይቷል፡፡
ግድቡን አጠናቆ አርሶ አደሩን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ በ202 ሚሊየን ብር ግንባታውን ለማጠናቀቅ ለተቋራጭ ሰጥቷል።
የደራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ሸጋው ሹሜ እና የደራ ወረዳ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ወልደሰንበት አበበ፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን ብለዋል፡፡
የተፈጠረበትን መጓተት ቀርፎ በሚፈታ መንገድ እንዲጠናቀቅና ተጠቃሚ አርሶ አደሮችንም እንዲያካትት ተደርጎ ዲዛይኑ መነደፉን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት መምሪያ ኀላፊ በልእስቲ ፍስሐ ናቸው፡፡
የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየልኝ መሣፍንት የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ያለፈው ስህተት እንዳይደገም ተደጋጋሚ ጥናት መደረጉን የጠቀሱት አቶ አየልኝ፤ ቀሪ ሥራዎችም በትኩረት እንደሚጠናቀቁ ገልጸዋል፡፡
ያልተጠናቀቀው ግድብ 150 ሄክታር የማልማት አቅም የነበረው ሲሆን ተሻሽሎ ሲገነባ ወደ 204 ሄክታር መሬት እንደሚያለማ ይጠበቃል፡፡ የግንባታ ውሉ ለአባይ ኮንስትራክሽን ድርጅት የተሰጠው ይሄው ግድብ በሚቀጥለው ዓመት ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀምርም የቢሮው ኀላፊ ተናግረዋል።
የቀጣይ ማጠናቀቂያ ሥራዎች ላይ ከቀበሌ እስከ ዞን አመራሮች በተገኙበት ጉብኝትና ውይይት ተደርጓል፡፡
የገልዳ ወንዝ የመስኖ ግድብ በዞኑ ከሚሠሩ 3 ከፍተኛ የመስኖ አውታሮች ውስጥ አንዱ ነው
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የሊቃውንት መገናኛ፣ የደጋጎች መማፀኛ”
Next articleበመስኖ ስንዴን ማልማት