እነዚህ ደግ ሕዝቦች በጓሯቸው የልጆቻቸውን ገዳይ እያሳደጉ ነው፡፡

324

በዚሁ 2012 ዓ.ም መጀመሪያ በሦስተኛው ቀን አንድ ስልጠና ላይ የመገኘት ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ ስልጠናው የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ዕቅዱን ለመገናኛ ብዙኃን ማስተዋወቅና በሙያቸው እገዛ እንዲያደርጉ የሚያግዝም ነበር፡፡ በስልጠናው በጤናው ዘርፍ ያሉ ፈተናዎችንና መልካም አጋጣሚዎች ተብራርተውበት ነበር፡፡ በተለይም የሱስ መስፋፋትን ለመግታት ቢሮው ያቀደውንና ችግሩን ለመከላከል የሚወሰደው እርምጃ ይበል ያሰኛል፡፡
ለአብነት ማንኛውም አጫሽ በሆቴል ቤት፣ በመዝናኛ ቦታዎች፣ በትራንስፖርት ጣቢያዎች፣ በመስሪያ ቤቶችና ሕዝብ በሚሰበሰብበት ማንኛውም ቦታ ሲጋራ ማጨስ የሚከለክለውን ሕግ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ማጨስ የሚቻለውም ከእነዚህ ቦታዎች 10 ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከ10 ሜትር ሲርቅ ወደ ሌላ መሥሪያ ቤትና ሕዝብ ወደ ሚሰበሰብበት የሚደርስ ከሆነ ማጨስ አይቻልም፡፡ ሲያጨስ ቢገኝ በአዋጁ መሠረት ቅጣት ይተላለፍበታል፡፡
ብዙዎቻችን በተግባር እንዲፈጸም የተጫወትነው ሚና የጎላ ባለመሆኑ አሁንም ተጠቂዎች ሆነናል፡፡ የዘርፉ ምሁራን ከአጫሹ ይልቅ ሲጨስ የሚሸተው ሰው ላይ ጉዳቱ ከፍ እንደሚል ይገልጻሉ፡፡ በወቅቱ ሰልጠናውን የሰጡን የክልሉ የጤና ጥበቃ ቢሮ ባለሙያዎች ሱስን ለመዋጋት ከምንጊዜውም በተለየ በትኩረት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም ሕጉና መመሪያው በሚፈቅደው ልክ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት እና እየተከታተሉ በማጋለጥ እገዛ እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል፡፡
ስልጠናውን በወሰድኩ ወር ባልሞላ ጊዜ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር ለሥራ ወደ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አቀናሁ፡፡ በብሔረሰብ አስተዳድሩ ርዕሰ ከተማ ኬሚሴ በቅርብ ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው የደዋ ጨፋ ወረዳ ቢላቻ ቀበሌ ነው፤ ለዚህ ትዝብት መነሻ የሆነ ጉዳይ የገጠመኝ፡፡
በቀበሌዋ በርከት ያሉ ማሳዎች በጫት ተክል ተሸፍነዋል፡፡ ሁሉንም እየቃኘሁ የበለጠ ወደ ገጠሩ ስጠጋ ለዓይኔ አዲስ የሆነ ነገር በየጓሮዎቹ ተዘርቶ ተመለከትኩ፡፡ ቅጠሉ ሰፋፊ ነው፡፡ ጥቅል ጎመን ይመስላል ነገር ግን ከጥቅል ጎመን ጋር ስለምንተዋወቅ ጥቅል ጎመን እንዳልሆነ ለራሴ አረጋገጥኩ፡፡ አካሄዴ ለሌላ ተግባር ቢሆንም የዚያን አዝርዕት ስምና ጥቅም ሳላውቅ መመለስ ግን አልፈለኩም፡፡ ጓሮዎችን እየቃኘሁ በርከት ያሉ ቤቶች ወደ ተሠሩበት አካባቢ ተጠጋሁ፡፡
ከቤቶቹ በር በአልጋና ሸራ የተሰጣ ተድበልብሎ የተሠራ ቅመም ነገር ተመለከትኩ፡፡ ይሄም ትኩረቴን ሳበኝ፡፡ መጀመሪያ የሄድኩበትን ተግባር ስፈጽም ድቡልቡሉን እና በጓሮው የተዘራውን ተክል ምንነት ጠየኩ፡፡ ተድበልብሎ የተሰጣውን ቅመም መሰል ነገር በደንብ እንዲደርቅ የሚያገላብጥ አንድ ወጣት “ትንባሆ ይባላል” አለኝ፡፡ የእውነት ደንግጫለሁ ጆሮዬን አላመንኩም ምን? አልኩት በአደነጋገጤ ግርምት ፈጥሮበት ፈገግ እያለ፡፡ “ትንባሆ ይባላል ትንባሆ አታውቅም?” እንዴ አለኝ፡፡ እረ አውቃለሁ፡፡ የት አገኘኸው? አልኩ አከታትዬ፤ የልጁ እናት ከኩሽና እየወጡ “ከጓሮ ነው እንጂ ከዬት ይገኛል አሉ፡፡” እሳቸውም ፈገግ እያሉ፡፡
ያ ሰፊው ቅጠልም ትንባሆ እንደሆነ እዛው በቆምኩበት አረዱኝ፡፡ እና ትንባሆ ማምረት ይቻላል ማለት ነው እዚህ አካባቢ? “ታዲያ ተችሎ ነዋ እዚህ ይህን ያገኘኸው አሁን እንዳውም ገበያው ጥሩ ስለሆነ ሌላ አትክልት ከመትከል ይህን መትከል ያዋጣል፡፡ አንዷን ጥቅል እስከ 15 ብር ድረስ ስለምንሸጣት ጥሩ ገበያ ነው ያለው” አለኝ፡፡ “የሚሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ” እንዲሉ አበው ሲጋራ እና ሌሎች አደገኛ ሱሶችን የሚጠቀም ሰው እንዳይኖር እንሠራለን ያለው የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ እንጀቴን በላው፡፡
በአካባቢው በርካታ አርሶ አደሮች ትንባሆን ይዘሩታል፡፡ ከምርቱም ከመሸጥ ባለፈ ራሳቸውም ያጨሳሉ፡፡ በስፍራው ያገኘኋቸው አርሶ አደሮች እንደነገሩኝ ለትንባሆ አዲስ የሆነ ሰው በጥርሱ ሲነክስ ሰክሮ እስከመውደቅ ይደርሳል፡፡ የት ወስደው እንደሚሸጡትም ጠይቄ ነበር፡፡ ከተማ ወስደው ለነጋዴዎች እንደሚያስረክቡ ነገረውኛል፡፡ ይህ አይደለም የገረመኝ አርሶ አደሮቹ ትንባሆውን በጥርሳቸው ሲይዙ ለሥራ እንደሚያነቃቃቸውና ፈጣን እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸውም ነግረውኛል፡፡ “ለጤና ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም” ሲሉም በድፍረት ይናገራሉ፡፡
በሌላ መልኩ የጀርመኑ የመረጃ አውታር ዶቼ ቬይለ ትንባሆን በማንኛውም መልኩ መጠቀም እና በተዘዋዋሪ ለጭሱ መጋለጥ ለልብ ሕመም የሚዳርግ ዋና ምክንያት መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት መግለጫን ጠቅሶ ዘግቧል። የልብ ድካም እንዲሁም የደም ዝውውር መታወክ ወይም ስትሮክ በመላው ዓለም በዓመት ሦስት ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ እንደሚፈጅም ዘርዝሯል። ትንባሆ በጥቅሉ በየዓመቱ ከሰባት ሚሊዮን ለሚበልጥ ሕዝብ ሕይወት ማለፍ ምክንያት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ ቻይና እና ሕንድ ውስጥ አብዛኞቹ አጫሾች ይህን እንደማያውቁ ዘገባው ያመላክታል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት የበሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል ዓለም አቀፍ የትንባሆ አጠቃቀም ቅኝት በግልፅ እንዳሳየው ማጨስ የደም ዝውውር መታወክን እንደሚያስከትል የማያምኑ አዋቂዎች ብዛት 73 በመቶ ይደርሳል። 61 በመቶዎቹ ደግሞ ማጨስ የልብ ድካም አደጋን እንደሚያባብስ ግንዛቤው የላቸውም።
የኛ ሀገር አርሶ አደር ደግሞ ጭራሽ የገቢ ምንጭ አድርጎ ማሳውን በትንባሆ ሸፍኖታል፡፡ እኔ ግን እንዲህ አልኩ፤ ‹እነዚህ ደግ ሕዝቦች በጓሯቸው የልጆቻቸውን ገዳይ እያሳደጉ ነው›፡፡ ጎጂ ስለመሆኑ የገባቸው እንዳችም ነገር የለም፡፡ የሚያስገኘው ገንዘብ እንጂ የሚያመጣው የኑሮ መቃወስ ትዝ አላላቸውም፡፡ ስለጉዳዩ ያወራሁት የአካባቢው የግብርና ባለሙያም ስለትንባሆ ጎጂነት አርሶ አደሩ መስማት እንደማይፈልግ ነግሮኛል፡፡ በእርግጥ አርሶ አደሮቹም “የተባረከ አትክልት ነው፤ ልጅ ለማስተማሪያና ለሌሎች ጉዳዮች ጠቅሞናል” ብለውኛል፡፡
በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ሀሚድ መኮንን በክልሉ ሱስን ለማስቀረት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ በአካባቢው ለረጅም ዓመታት የጫትና የትንባሆ ምርት ሲመረት ቆይቷል፡፡ ያለውን ግንዛቤ ለመቀየር ብዙ ሥራዎች ይጠበቃሉ፡፡ ምርቱን እንዲያቆሙ የሚያግዝ አዋጅ ባለመኖሩ ቀስ በቀስ ስልጠና በመስጠት ከምርቱ እንዲወጡ ለማድረግ እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡ ምርቱን ሊተካ የሚችል ጠቃሚ ምርት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለማቅረብም እንደሚሠራ ነግረውኛል፡፡ በትምባሆ ላይ የተሠራው ሥራ ያን ያክል አመረቂ እንዳልሆነ ነው የተረዳሁት፡፡
ዓለም ላይ ብዙ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በሱስ ምክንያት ከመደበኛ ኑሯቸው ተስተጓጉለዋል፡፡ በርካቶች የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ገሚሶች በዚሁ ጦስ ምክንያት ያለ ዕድሜያቸው ሞተዋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም የችግሩን አስከፊነት የማስገንዘብ ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

Previous articleበለንደን የሚኖሩ ኢትዮጵያውንና አጋር አካላት ለተፈናቃዮች ማቋቋሚያ ድጋፍ አደረጉ፡፡
Next articleየአየር ንብረት ለውጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሚያስፈልግበት ደረጃ መድረሱን ተመራማሪዎች አስታወቁ፡፡