የድርቅ አደጋ ትንበያዎችን ተከትሎ በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

96
ባሕር ዳር: መጋቢት 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ጊዜያት በክልሉ የተፈጠሩት ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች የሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን ቁጥር እንዲጨምር አድርጎታል፡፡ ጦርነት እና ግጭት በፈጠረው መፈናቀል የዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንደተጠበቀ ሆኖ ባለፈው ዓመት የክረምቱ ዝናብ ዘግይቶ በገባባቸው እና ቀድሞ በወጣባቸው የተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ፈላጊዎች ሆነዋል፡፡
በምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ከወራት በፊት የተከሰተው የድርቅ አደጋ ወደ ሰሜን ምሥራቅ እና መሃል ሀገር የመስፋፋት እድል ይኖረዋል የሚለውን ትንበያ ተከትሎም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የድርቅ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ተሰግቷል፡፡ የድርቅ አደጋው ከተከሰተ ከፍተኛ የሆነ የውኃ እጥረት ስለሚፈጠር በንጹህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ መስኖ ልማት፣ ሰብል ልማት እና እንስሳት ሃብት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
የድርቅ አደጋ ትንበያዎችን እና ሌሎች ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለውን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ፍላጎት የሚመልስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ በክልሉ ያደሩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እንዳሉ ጠቅሰው በቂ ባይሆንም የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ በምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው የድርቅ አደጋ ወደ ሰሜን ምሥራቅ እና መሃል ኢትዮጵያ ሊሰፋ ይችላል የሚል ስጋት እና ትንበያ አለ ያሉት ዳይሬክተሩ በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ከ35 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ በጀት መጠባበቂያ የምግብ እህል ክምችት በመጋዘን እንዲኖር ለማድረግ እየሠራ ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጡ ቅድመ ትንበያዎችን ተከትሎ የቀረበው የተጨማሪ በጀት ጥያቄም በክልሉ መንግሥት አጥጋቢ ምላሽ አግኝቷል ብለዋል፡፡
ነገር ግን በትንበያው መሰረት የድርቅ አደጋው የሚከሰት ከሆነ ከሌሎች በተገኘው ልምድ መሰረት ከፍተኛ የውኃ አቅርቦት እጥረት ስለሚኖር የሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፡፡ የክልሉ ውኃና ኢነርጅ ቢሮ አማራጭ የውኃ አቅርቦቶችን ማየት፣ የክልሉ ግብርና ቢሮ በፍጥነት የሚደርሱ ሰብሎችን በአማራጭነት መጠቀም እና የክልሉ እንስሳት ሃብት ልማት ኤጀንሲ የእንስሳት መኖ አቅርቦት እና አማራጭ መፍትሔዎችን ማየት ይጠይቃቸዋል ብለዋል፡፡
በተለይም የድርቅ አደጋ ሲከሰት በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ የሚሆኑት እንስሳቶች ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ አደጋው ሲከሰት በዝቅተኛ ዋጋ ከመሸጥ አርሶ አደሩ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማዘጋጀትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በጊዜያዊነት ማቆየት፣ ሽጦ ገንዘቡን እንዲይዝ እና አደጋው ሲያልፍ አቅርቦት ተመቻችቶለት ግዥ እንዲፈጽም እና ከተቻለም በቂ መኖ ማከማቸት እንዲችል ማድረግን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በጋራ መሥራት የሚያስችል እቅድ አለው? ሲል አሚኮ ላነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ዳይሬክተሩ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ለጋራ አሠራር ምቹ ባይሆንም ካለው ስጋት አንጻር በቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ግብረ ኀይል በኩል ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦች እና ምክክሮች ይደረጋሉ ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
Previous articleየጣና ሐይቅን ደኅንነት ለመጠበቅ በአካባቢው ያሉ ረግረጋማ ቦታዎችን ማልማት አስፈላጊ መኾኑ ተገለጸ።
Next article“የሊቃውንት መገናኛ፣ የደጋጎች መማፀኛ”