
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ በጣና ሐይቅ እና በአካባቢው ላይ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱ የገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ጌታቸው ጀንበር (ዶ.ር) በጣና ሐይቅ ላይ እየተስፋፋ ያለው እንቦጭ አረም እና ወደ ሐይቁ በጎርፍ አማካኝነት የሚገቡ ኬሚካሎች ሐይቁ ላይ ጉዳት እያደረሱ መኾኑን ገልጸዋል።
ዶክተር ጌታቸው፤ በጣና ሐይቅ ላይ እየተስፋፋ ያለው እንቦጭ እና በጎርፍ አማካኝነት የሚገቡ ኬሚካሎች ሐይቁ ላይ ጉዳት እያደረሱ መኾናቸውን አንስተዋል።
ጉዳቱን ለመከላከል የጣና ሐይቅ እና በአካባቢው ያሉ ረግረጋማ ቦታዎችን ማልማት አስፈላጊ መኾኑም በውይይቱ ተነስቷል።
ጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አያሌው ወንዴ (ዶ.ር) እንዳሉት 36 ቀበሌዎች በእንቦጭ ተወረዋል። 33ቱ በኅብረተሰብ ተሳትፎ የሚወገዱ ናቸው። ነገር ግን በኅብረተሰብ ተሳትፎ የሚሠራው የማጽዳት እና ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባለመቻሉ እምቦጭ አሁንም የጣና ሥጋት ነው ብለዋል።አርሶ አደሩ ለሥራው ባለቤት ከዚያም በላይ ተጠቃሚ መኾን እንዲችል ኀላፊነትን መውሰድ አለበት ብለዋል።
የጣና ቤተሠብ ተቋቁሞ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን የተናገሩት ዶክተር አያሌው፤ ጣናን ተጠግተው የሚለሙ ልማቶች እና የሚገነቡ ግንባታዎች የጣናን ኅልውና በማይጎዳ መልኩ መኾን እንዳለበት አጥብቀን እንሠራለን ብለዋል።
ጉዳት ያደረሱ ሆቴሎች ላይ ቅጣት እየተወሰደ መኾኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ ቀጣይ በጣና ዙሪያ ላይ ለማልማት የተዘጋጁ ባለሃብቶች እንዲሁም ካሁን በፊት የገነቡ ባለሀብቶች ይህንን አጥብቀው መያዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!