“ኢትዮጵያ የተወሰኑ ብሔሮች ሀገር ብቻ ሳትኾን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አንጡራ ሀብት ናት” የተከበሩ ዶክተር ከፈና ኢፍ

89
ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባላትም ያለፉትን ሥድስት ወራት አፈጻጸም መሠረት በማድረግ እና ከመራጭ ተመራጭ ውይይቶች ማግሥት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከገጠሟት አሁናዊ ችግሮች መካከል ጦርነት፣ የእርስ በእርስ ግጭት፣ መፈናቀል እና የኑሮ ውድነት እንደኾነ ትኩርት ሰጥተው የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል፡፡
የኑሮ ውድነት ሰላም እና ደኅንነት ለራቀው ሕዝብ ተጨማሪ ፈተና እንደኾነም ተነስቷል፡፡ የመሠረተ ልማት ግንባታ እና ፍትሐዊ ተደራሽነት በእንደራሴዎቹ ትኩረት የተሰጠው ጥያቄ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘመናት ድርቅ እና ርሃብ፣ ጦርነት እና ግጭት፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት ከፈጠሩባት ፈተናዎች ጀርባ ውስጣዊ ሴራዎችም ነበሩበት ያሉት የምክር ቤቱ አባል ዶክተር ከፈና ኢፍ ኢትዮጵያ እና ጦርነት ሳይለያዩ እንዲቆዩ አድርጓል ብለዋል፡፡
አሁናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰንኮፍም ከውጭው ጫና ይልቅ ከውስጥ የሚፈልቀው ልዩነት አደገኛ እየኾነ መጥቷል ነው ያሉት፡፡ ዶክተር ከፈና ኢትዮጵያዊያን በደም የተጋመዱ በጋብቻ የተዋለዱ ሕዝቦች ኾነው ሳለ በብሔር ፖለቲካ መንጠላጠል እና የኢትዮጵያን ሰላም ውላ ማደር የማይፈልጉ ርካሽ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያን እያደሟት ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት ኢትዮጵያን ከእንዲህ አይነት ፖለቲከኞች እጅ መታደግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ “ኢትዮጵያ የተወሰኑ ብሔሮች ሀገር ብቻ ሳትኾን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አንጡራ ሀብት ናት” ያሉት የተከበሩ ዶክተር ከፈና በገዥው ፓርቲ እና በተፎካካሪ ድርጅቶች ውስጥ ተሰግስገው የሕዝብ እና ሀገር ሰላምን የሚንዱ ኅይሎች ተለይተው እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡ ሠላምን የማይመርጥ ኢትዮጵያዊ ካለ ከውጭ ኅይሎች ጫና እና ጣልቃ ገብነት ያለነሰ ሀገራዊ ጉዳት ስላለው ትኩረት ይሰጠው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የብሔር ፖለቲካ እና የዘር አሰላለፍ ለአሁናዊ የሀገሪቱ ችግሮች መንስኤ እየሆኑ መጥተዋል” የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
Next article“ለሠላም የምንሠራው የድህረ ግጭት አውድ ጫና ውስጥ ኾነን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)