በለንደን የሚኖሩ ኢትዮጵያውንና አጋር አካላት ለተፈናቃዮች ማቋቋሚያ ድጋፍ አደረጉ፡፡

162

ለተፈናቃዮች የሚደረገው ዘላቂ ማቋቋም ተጠናክሮ መቀጠሉን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለፀ። በለንደን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና አጋር አካላት በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ337 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።

በለንደን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተወካይ ወይዘሮ ባንችአምላክ ይልማ ተፈናቃዮችን በቋሚነት ለመደገፍ በሚደረገው ርብርብ በለንደን የሚገኙ ተወላጆችና አጋሮች ከ337 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

በእንግሊዝ ለንደን የሚገኙ ዜጎች ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር በክልሉ ጠንካራ አንድነት እንዲፈጠር በሐሳብ ለመርዳት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር አማረ ክንዴ ከለንደን በተጨማሪ በውጭ ያሉ ዜጎች ያደረጉትን ድጋፍ አመሥግነው፤ ድጋፉ ለታለመለት ዓላማ እንደሚያውሉት ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ከተለያዮ ክልሎች እና በክልሉ ውስጥ የተፈናቀሉ ከ107ሺህ በላይ ዜጎች ነበሩ። ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ያስፈልግ ነበር። ባለፈው ዓመት በተደረገው የገቢ ማሰባሰብ 720 ሚሊዮን ብር ቃል ገብቶ 423 ሚሊዮን ብሩ መሰብሰብ መቻሉን ኮሚሽነር አማረ ተናግረዋል።

‹‹ከማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎችን 90 በመቶ በዘላቂነት አቋቁመናል›› ያሉት ኮሚሽነሩ ዕቅዱ እንዲሳካ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የሚደረጉ ድጋፎች በዘላቂነት ያልተቋቋሙ ተፈናቃዮችን ለመደገፍ የሚውል ነው። ባለፈው ዓመት ከኦሮሚያና ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች አብዛኞቹ አለመሄዳቸውን አቶ አማረ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ግርማ ተጫነ

Previous articleበ13 ወራት ውስጥ ግንባታው የተጠናቀቀዉ የአዲስ አበባ ‹ሲልክሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል›› ተመረቀ፡፡
Next articleእነዚህ ደግ ሕዝቦች በጓሯቸው የልጆቻቸውን ገዳይ እያሳደጉ ነው፡፡