
ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ሲጀመር የምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
የምክር ቤት አባላቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። የብሔር ፖለቲካ እና የዘር አሰላለፍ ለአሁናዊ የሀገሪቱ ችግሮች መንስኤ እየሆኑ መጥተዋል ያሉት የምክር ቤቱ አባላት መንግሥት በየደረጃው ያለውን የአስፈጻሚ አካል ሚና እና አሰላለፍ እንዲመለከትም ጠይቀዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተስተዋሉ ግጭቶችን እና ጦርነትን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥት የሄደበትን እርቀት በበጎ ጎኑ ያነሱት የምክር ቤቱ አባላት አፈጻጸሞቹ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ያጋጠሙ የሰላም ሳንካዎችን፣ መፈናቀሎችን እና የእርስ በእርስ ግጭቶችን ለማስቆም መንግሥት እየወሰደው ያለውን እርምጃ እንዲያብራሩላቸው ጠይቀዋል፡፡
ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ሕብረ ብሔራዊ ድርጅት ነኝ ቢልም በየጊዜው በክልል አስፈጻሚ አካላት የሚሰጡ ጎራ የለዩ መግለጫዎች በአስፈጻሚው አካላት የጎራ ልዩነቶች እንዳሉ የሚያመላክቱ ናቸው ያሉት የምክር ቤቱ አባላት የፌዴራል መንግሥት ችግሩን በዝምታ መመልከቱ ክፍተት እንደሆነ አንስተዋል፡፡
በፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላት ላይም ችግሩ ስለሚስተዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡበት ጠይቀዋል፡፡
ከጊዜ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም መንግሥት አስፈላጊ እርምጃዎችን እየወሰደ አይደለም ያሉት የምክር ቤቱ አባላት ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ፖለቲካዊ ችግሮችም አሉበት ነው ያሉት፡፡ በተለይም ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ ክልሎች በሚፈጠር መንገድ መዘጋት እና የተጓዦች መንገላታት ምርት ገበያ ላይ እንዳይወጣ ተደርጓል ብለዋል፡፡ መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሄደበትን መንገድ እንዲያብራሩላቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡
የመሠረተ ልማት ውስንነቶች፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ሠላም እና ደኅንነት፣ የሀገሪቱ ድንበሮች በአግባቡ አለመከበር እና በዜጎች እየደረሱ ያሉ ጉዳቶች፣ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የሚስተዋሉ የዜጎች መዋከብ፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ግድያ እና ዝርፊያ ተጠናክሮ መቀጠሉ የምክር ቤቱ አባላት እንዳሳሰባቸው በምክር ቤቱ አባላት በጥያቄ እየተነሱ ነው፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!