ለሠላማዊ ውይይት ዝግጁ መሆኑን የቅማንት የማንነትና ራስ አስተዳደር ይከበርልኝ ማዕከላዊ ኮሚቴ ገለፀ።

351

ኮሚቴው ሐሳቡን ያቀረበው በኢፌድሪ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልና በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ ከተመራው የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከአማራና ከቅማንት ሕዝብ ከተወጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በጭልጋ ወረዳ ሰራባ ከተማ በካሄዱት ውይይት ነው። በውይይቱ ከማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተወጣቱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የቅማንት የማንነትና ራስ አስተዳደር ይከበርልኝ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍቃዱ ማሞ ሠላም ቅድመ ሁኔታ ሊቀመጥለት የማይችል በመሆኑ አጥብቀው እንደሚፈልጉት ተናግረዋል። የቅማንት የማንነትና ራስ አስተዳደር ይከበርልኝ ጥያቄ የሁለቱ ወንድማማች ሕዝብ የግጭት መንስኤ መሆን እንደሌለበትም አስረድተዋል። በአካባቢው በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት መቆም እንዳለበትና ጉዳዩ በሠላማዊ መንገድ እስኪፈታ ድረስ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ከሚፈልጉ ማንኛውም አካላት ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ከዚህ በፊት አውጥቶት በነበረው የአቋም መግለጫ ‹በጠረጴዛ ዙሪያ እንነጋገር› ያለውንና ‹ሕዝብ ያነሳው ጥያቄ በሕዝብ ይሁንታ ሊፈታ ይገባል› የሚሉትን ሐሳቦች ኮሚቴው ተቀብሎት እንደነበርም ገልፀዋል። ‹‹እኛና እናንተ ሳንባባል በሕዝብም በመንግሥት መካከል ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የውይይት በር መከፈቱ አስፈላጊ በመሆኑም ኮሚቴው የቀረበውን የሠላም ጥሪ ተቀብሎታል፣ ለውይይትም ዝግጁ ነው›› ብለዋል።

ይሁን እንጅ በመድረኩም ‹‹የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ እናራምዳለን የሚሉ ሁለት ኮሚቴዎች እንዳሉና በሕዝቡ መካከል ልዩነት እየፈጠሩ ነው›› የሚል ሐሳብ ተነስቷልና ለቀጣይ ሠላማዊ ውይይቱ እንቅፋት ስላለመሆኑ ለአቶ ፍቃዱ ጥያቄ ተነስቷል። አቶ ፍቃዱ ሲመልሱም ‹‹ኮሚቴ ነን የሚሉት እኛ በሥነ ምግባር ያሰናበትናቸው ግለሰቦች ናቸው። በቀጣይ ሠላማዊ ሂደቱ እንቅፋት ሊፈጥሩ አይችሉም፤አንድ ሕጋዊ ኮሚቴ ነው ያለው። እሱም እኔ በሰብሳቢነት የምመራው ነው። ሕዝቡም ዕውቅና ሰጥቶት እየተንቀሳቀሰ መቆየቱ ይታወቃል›› ብለዋል አቶ ፍቃዱ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ ሠላማዊ ውይይቱ እንዲኖር በሐሳብ መነሳቱን አወድሰዋል። በቀጣይ ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር በተግባር ማረጋገጥ እንደሚገባም መክረዋል። የክልሉ መንግሥት ለተግባራዊነቱ እንደሚተጋም አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

Previous articleአፋር እና ሶማሌ ክልሎች ላይ የአንበጣውን የሕይወት ዑደት ማቋረጥ ካልተቻለ ስርጭቱ አሁን ካለበትም እንደሚጭምር የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleበ13 ወራት ውስጥ ግንባታው የተጠናቀቀዉ የአዲስ አበባ ‹ሲልክሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል›› ተመረቀ፡፡