
በ13 ወራት ውስጥ ግንባታው የተጠናቀቀዉ የአዲስ አበባ ‹ሲልክሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል›› ዓለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና በዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎች የተደራጀ ሆኖ ተመርቋል፡፡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ሁለገብና ልዩ ሐኪሞች (ስፔሻሊስት) ተመድበውለታል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የግል ባለሀብቶችን በጤናዉ ዘርፍ ለማሳተፍ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ ለመሆኑ ዶክተር ዋንግ ዣንዡ በተባሉ ቻይናዊ ባለሀብት የተገነባዉ ይህ ሆስፒታል አንዱ ማሳያእንደሆነም በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ተመላክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ሲልክሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ዋንግ ዣንዡ ሆስፒታሉ በአጭር ጊዜ እና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ እንዲጠናቀቅ የቡድኑ ቁርጠኝነት ታላቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው በመግለጽ ‹‹በጣም ደስ ብሎኛል፤ ድጋፍ ላደረጉልን ሁሉም ምሥጋና ማቅረብ አፈልጋለሁ፡፡ ሆስፒታሉ ዓለማቀፍ ደረጃዉን የጠበቀ ነዉ፡፡ ወደፊት አገልገሎታቸን ጥራት ያለዉ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንሠራለን›› ብለዋል፡፡
የኢፌድሪ ጤና ሚንስትር ዶክተር አሚር አማን ‹‹ይህ ሆስፒታል በመገንባቱ በአቅም ማነስ ምክንያት ወጭ ሀገር ሄደዉ መታከም ለማይችሉ ኢትዮጵያውን ታላቅ ዜና ነው፡፡ ከዚህ በተጭማሪ አቅም ኑሯቸዉም አገልገሎቱን ስለማያገኙ ብቻ ወደ ዉጭ የሚሄዱትን ታካሚዎችን በማስቀረት እና ወጫቸውን በመቆጠብ ታላቅ ሚና ይጫወታል›› ብለዋል፡፡
በጤናዉ ዘርፍ የግል ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ዉስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚፈልግና እንደሚያረታ ወደ ፊትም አብሮ ለመሥራት እና ለመረዳዳት ሚኒስቴሩና መንግሥት ዝግጁ መሆናቸውንም ዶክተር አሚር አማን ተናግረዋል፡፡
የቻይና ፈቃደኛ ሐኪሞች መሪ እና የቻይና ‹ኒዮሰርጅን› ማኅበር ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሊንግ ፌንግ ኢትዮጵያ ውስጥ በጤናዉ ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን ሰሠሩ እንደቆዩ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ሕሙማን የነጻ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠን ነዉ፡፡ የዚህ ሆስፒታል ግንባታም አቅም የሌላቸዉን ታካሚዎች መነሻ በማድረግ ጭምር ነው›› ብለዋል፡፡ ይህንን ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ያመለከቱት፡፡
በዚህ ወቅት 13 በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞች እንዳሉትም ተመላቷል፡፡ ዘጠኙ ከቻይና ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከሌሎች ሀገራት የተውጣጡ ናቸው፡፡ ‹‹በዚህ አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በርካታ ሕሙማንን ረድተናል፤ አጠናክረንም እንቀጥላለን፡፡ ይህ ታላቅ ሆስፒታል መገንባቱ ብዙ ታካሚዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንድረዳ ያደርገናል፡፡ ለጤና ባለሙያዎችም አቅም ግንባታ እንድናደርግ ይጠቅማል›› ነው ያሉት በጎ ፈቃደኞቹ፡፡
የቻይና በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና ንግድ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሚስ ሊዩ በበኩላቸዉ የኢትዮጵያ እና የቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት ሁሉን አቀፍ እና የቆየ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ የሕክምና መሣሪያዎች እጥረት እንዳለ እንረዳለን፤ ይሄን ችግር ለመፍታትም ትብብራችን አጠናክረን እንቀጥላለን›› ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ