
ባሕር ዳር:መጋቢት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጣልያናዊው አሰልጣኝ አንቶንዮ ኮንቴ ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ቶተንሃም አሰልጣኝነታቸው መነሳታቸውን ክለቡ አስታውቋል፡፡
የ53 ዓመቱ ጎልማሳ ጣሊያናዊው አሰልጣኝ አንቶንዮ ኮንቴ ለ16 ወራት ከቶተንሀም ጋር የነበራቸውን ቆይታ በስምምነት ቋጭተውታል ተብሏል፡፡ ከጁቬንቱስ፣ ቼልሲ፣ ኢንተር ሚላን እና ቶተንሃም ጋር በአሰልጣኝነት ያገለገሉት ኮንቴ የቶተንሃም ቆይታቸው ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገበበት ነበር ነው የተባለው፡፡
በቅርቡ ከሳውዝአምፐተን ጋር አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የክለቡን ተጫዎቾች “ራስ ወዳድ” ሲሉ ተችተዋቸዋል፡፡
ከቼልሲ፣ ጁቬንቱስ እና ኢንተር ሚላን ጋር የሊግ ዋንጫዎችን ያነሱት ጣሊያናዊው አሰልጣን አንቶኒዮ ኮንቴ ወደ ቆተንሃም ያቀኑት ኑኖ ኢስፔሪቶ ሳንቶ መባረራቸውን ተከትሎ በሕዳር 2021 ነበር።
አሰልጣኝ አንቶንዮ ኮንቴ መሰናበታቸውን ተከትሎ ምክትል አሰልጣኝ የነበሩት ክርስቲያን ስቴሊኒ ክለቡን እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት እንደሚመሩት ተገልጿል። ቶተንሃም በፕሪሜርሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አራተኛ ላይ ቢቀመጥም ከሁሉም የዋንጫ ፉክክሮች ውጭ ሆኗል፡፡
ጊዜያዊ አሰልጣኙ ክርስቲያን ስቴሊኒ በቀሪ 10 ጨዋታዎች በእጃቸው ያለውን የቻምፒዮንስ ሊግ ቦታ አስጠብቆ የውድድር ዓመቱን ለማጠናቀቅ እንሠራለን ማለታቸውን ቢቢሲ ስፖርት በገጹ አስነብቧል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!