የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ምዝገባ ከመጋቢት 20 እስከ ሚያዚያ 15 ይካሄዳል።

1561
ባሕር ዳር :መጋቢት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የ2015 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና ምዝገባ ከመጋቢት 20 እስከ ሚያዚያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት በመግለጫው አስታወቀ።
መግለጫውን የሰጡት የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ.ር) የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ምዝገባ ከመጋቢት 20 እስከ ሚያዝያ 15 ድረስ በበይነ-መረብ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
ከዚህ በፊት ይታዩ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ የተሻሉ አሰራሮችን በመከተል ምዝገባው እንደሚካሄድ ተገልጿል።
አገልግሎቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ባለፉት ጊዜያት በፈተና አሰጣጡ ሂደት የአፈፃፀም ችግር በምዝገባ ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩን አስታውቋል።
በወጣው የምዝገባ መርሐ-ግብር አለመመዝገብ ፣ የመመዝገቢያ ግብዓቶችን አሟልቶ አለመገኘት እና የምዝገባ ጊዜ ካለፈ በኋላ መምጣት በተመዝጋቢዎች ዘንድ የታየ ጉድለት ነበር ተብሏል።
በመዝጋቢዎች ደግሞ ለተመዝጋቢዎች ተገቢውን መረጃ አለመስጠት በትምህር ቤቱ ርዕሰ መምህር የተሰጣቸውን መመሪያ ባለመከተል ምዝገባ ማካሄድ እንዲሁም የተፈታኙን የግል ሁኔታ በተገቢው መንገድ አለመሙላት የታዩ ጉድለቶች መሆናቸውም ነው የተነገረው።
ችግሮቹ በፈፃሚዎች ፣ በተመዝጋቢዎች ፣ በመዝጋቢዎች እና በትምህርት ቤቶች በጉልህ መታየታቸውም ነው የተመለከተው።ይሄ በዚህ ዓመት እንዳይከሰት ስራዎች ተሰርተዋል ተብሏል፡፡
ምዝገባው በበይነ መረብ የሚካሄድ በመሆኑ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸውም ተብሏል።
በዚህ መሰረት መደበኛ እና የማታ ተማሪዎች በሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በመገኘት ምዝገባ ሚካሄድ የሚችሉ ሲሆን ለድጋሚ እና ለርቀት ትምህርት ተከታታዮች በተመረጡ የወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች በበይነ መረብ በቀጥታ ምዝገባ የሚያካሂዱ ይሆናል ተብሏል።
ከምዝገባ በኋላ የሚቀርቡ የሥም፣ የፆታ፣ የዕይታ፣ የፎቶ እና የትምህርት መሥክ ማስተካከያ ጥያቄዎች ተቀባይነት እንደማይኖራቸውም የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቋል።ከዚህም በተጨማሪ በተመደበው ቀን ያልተመዘገበ ማንኛውም ተፈታኝ ለፈተና እንደማይቀመጥም ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው።
ዘጋቢ፦ራሄል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleእልፍኝ ከቤተሰብ መሐል:- ድንበር ያልገደበው ደግነት
Next articleየሰሜን ለንደኑ ክለብ ቶተንሃም አሰልጣኝ አንቶንዮ ኮንቴን አሰናብቷል፡፡