
ባሕር ዳር :መጋቢት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር መንገድ ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሳሙኤል ወርቅነህ እንደነገሩን የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር በጥናት ታግዞ በከተማዋ ያለውን የመንገድ ችግር ለመፍታ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶችን እየገነባ መሆኑን ገልጿል፡፡
ምክትል ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር በአራት ፕሮጀክቶች የከተማ አስፓልት መንገድ ሥራ እያከናወነ ነው፡
የመንገድ ፕሮጀክቶቹ 22 ነጥብ 17 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡ መንገዶቹ 3 ነጥብ 548 ቢሊዮን ብር እንደተበጀተላቸው ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከሚሠራቸው መንገዶች መካከል ከኤርፖርት ተነስቶ በማርዳ እብነበረድ የሚሄደው የመንገድ ፕሮጀክት ይገኝበታል ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ፕሮጀክቱ 8 ነጥብ 5 ኪሎሜትር የሚሸፍን እንደኾነ አብራርተዋል፡፡ አቶ ሳሙኤል መንገዱ ደረጃውን የጠበቀ እና 40 ሜትር የመንገድ ስፋት ያለው ስለመኾኑም ነግረውናል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት ላይ የአማራ መንገድ ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ በኮንትራክተርነት ሲሠራ በማማከር ደግሞ አማራ ዲዛይን ቁጥጥር እየተሳተፈ ነው፡፡
ሌላው የመንገድ ፕሮጀክት ዘንዘልማ (ዲያስፖራ) አካባቢ የሚሠራ የአስፋልት መንገድ ሲኾን 3 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተበጀተለት ይህ የመንገድ ሥራ አስፓልት በማልበስ ሥራ ላይም ይገኛል፡፡ በዚህ ዓመት ከሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ እንደኾነም ምክትል ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡
ከዓባይ ማዶ ተነስቶ የጭንብልን ወንዝ አቋርጦ ከአዲሱ አስፋልት መንገድ ጋር በማገናኘት ወደ ምድረገነት የሚያደርስ መንገድ ሌላው የከተማ አስተዳደሩ የአስፋልት መንገድ ሥራ ነው፡፡ ይህም አጋዥ መንገድ ሲኾን 1 ነጥብ 77 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ አጋዥ መንገድ 321 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለታል ነው ያሉት፡፡
በፋሲሎ ኪዳነምህረት አቋርጦ ወደ ቁልቋል የሚሄደው 7 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር መንገድ ሌላው የከተማ አሥተዳደሩ የአስፋልት መንገድ ሥራ ነው፡፡ 478 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት እየተሠራ ያለ መንገድ ነው፡፡
ከባለእግዚአብሄር መንገድ ወደ ልደታ ተገንጥሎ አዲሱ ምሪት የሚሄደው መንገድ ሌላው ከተማ አሥተዳደሩ የሚሠራው መንገድ ነው፡፡ ይህም መንገድ 1ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲኾን መንገዱ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ መንገዱ የመብራት እና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች እንደሚቀሩት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ነግረውናል፡፡
ምክትል ሥራ አስኪያጁ ሳሙኤል እንዳሉት መንገዶቹ ሲጠናቀቁ የባሕር ዳር ከተማን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የበለጠ እንደሚያሳድገው አስረድተዋል፡፡ መንገዶቹ ከቀን ሠራተኛ ጀምሮ እስከ ትልልቅ የሙያ ባለቤቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉም ምክትል ሥራ አስኪያጁ ነግረውናል፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!