
ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም እና የፀጥታ ችግሮች እንዲሁም የኑሮ ውድነት መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች መሆናቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሠረት ኃይሌ ተናገሩ።
የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታዋ የምክር ቤቱ አባላት ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ባደርጓቸው ውይይቶች ላይ ተነሥተዋል ያላቿውን ጥያቄዎች ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ነው።
የውይይት መድረኩ በ347 የምርጫ ክልሎች መካሄዱን በማንሣትም የዜጎች ከቦታ ቦታ በነፃነት የመዘዋወር ሕገመንግሥታዊ መብቶቻቸው አለመጠበቁ፣ በየጊዜው የሚያገረሸው ግጭት ሊቆም አለመቻሉ እና የሰው ሕይወት እና ንብረት መጥፋቱ፣ ለዚህም ዘላቂ መፍትሔ አለመሰጠቱ የብዙኃኑ ጥያቄዎች ናቸው ብለዋል።
በሌላ በኩል በየዕለቱ እየጨመረ የሚገኘው የሸቀጣ ሸቀጥ እና የፍጆታ ዕቃ ዋጋ መናር የፈጠረው የኑሮ ውድነት የኅብረተሰቡ ሌላኛው ፈተና መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት።
የተነሡ ጥያቄዎች በውይይቱ ወቅት የተሰጣቸው ምላሽ የምክር ቤቱ አባላትንም ሆነ ሕዝቡን ያላረኩ መሆናቸውን በማንሳትም በዛሬው ውይይት የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ምላሽ እንደሚሰጡባቸው አሳውቀዋል። መረጃው የኢቢሲ ነው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!