

ባሕር ዳር :መጋቢት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ አላምኔ ታደለ ይባላሉ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋዳሞት ወረዳ ድኩል ካና ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ወይዘሮ አላምኔ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አባል ከኾኑ 3 ዓመት አስቆጥረዋል። የጤና መድኅን አባል በመሆናቸው ብዙ ጊዜ ሕክምናም አግኝተዋል። አንድ ጊዜ በከፈሉት ገንዘብ ከነቤተሠባቸው ዓመቱን ሙሉ በመታከማቸው ወጪአቸውን እንደቀነሰላቸውም ነግረውናል።
ወይዘሮ አላምኔ “አኹን አንዳንድ መድኃኒቶች ጤና ጣቢያው ላይ የሉም፣ ከውጭ ገዝታችኹ አምጡ እየተባልን ነው። አሁን መድኃኒት የለም በመባሉ በራሳችን አቅም መታከም አልቻልነም” ብለዋል። ካሁን በፊት ከውጭ ለሚገዙት መድኃኒት በጤና ጣቢያው ተመን ይከፈል እንደነበርም ጠቅሰዋል። የመድኃኒት እጥረት አለ። ጤና ጣቢያው ላይ መድኃኒት እየቀረበ አይደለም። በተጀመረበት አግባብ ቢሄድ ተጠቃሚ እንኾናለን ብለውናል።
አርሶ አደር ገበያው ሞላ በደጋዳሞት ወረዳ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ የጤና መድኅን አባል ከኾኑ ሁለት ዓመት አልፏቸዋል። አርሶ አደር ገበያው የጤና መድኅን መክፈል በመጀመራቸው እሳቸውም ኾነ ቤተሠቦቻቸው በአግባቡ እየታከሙ መቆየታቸውን አስረድተዋል።
አሁን ላይ ግን በተደጋጋሚ አገልግሎት ለማግኘት ቢመጡም መድኀኒት የለም እየተባሉ ከግል እንዲገዙ መደረጉን ተናግረዋል። አርሶአደር ገበያው አገልግሎት አሠጣጡ እንዲስተካከልም ጠይቀዋል። መድኃኒት የለም መባሉ እና አሠራሩ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል።
በደጋ ዳሞት ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደመላሽ መኮንን ችግሩ መኖሩን ገልጸው ችግሩን ለመቅረፍ ከሦስተኛ ወገን ፋርማሲ መፈቀዱን ተናግረዋል። በወረዳው አምስት ጤና ጣቢያዎች እና አንድ ሆስፒታል እንዲኹም 13 የግል የጤና ተቋማት ውል ወስደው አገልግሎት እየሠጡ ነው ብለዋል። ጤና ጣቢያው ላይ በገጠመ የመድኃኒት እጥረት ኹሉም አገልግሎት እየሠጡ እንዳልሆነ ነው የነገሩን።
በ2013 ዓ.ም ከአባላቱ በቂ የአባልነት መዋጮ ባለመሰብሰቡ ኪሳራ ገጥሞን ነበር በዚህም ወጭውን መሸፈን ባለመቻላችን ችግሩ ተከስቷል ብለዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ደሳለኝ ዳምጤ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም ተቀዛቅዞ የነበረው የጤና መድኅን የክፍያ ሥርዓት ችግሩ እንዲከሰት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የጤና መድኅን አባል መኾን ሌሎችን መተባበር እንደሆነም ሊታወቅ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የዞኑ ነዋሪዎች ክፍያ ባለመክፈላቸው በአንዳንድ አካባቢች የመድኃኒት እጥረት መከሰቱን አንስተዋል፡፡
መከላከልን እና አክሞ ማዳንን መሠረት ያደረገው የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅፋቶች ተፈጥረው ነበር ያሉት ምክትል ኀላፊው ችግሮችን ለመቅረፍ አዳዲስ አባላትን የማፍራት ጉዳይ በተከታታይ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
በሁሉም ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች ላይ መድኃኒት በበቂ መጠን እንዲኖር እና አባላቱ በሚፈለገው ልክ አገልግሎት እንዲያገኝ እየሠሩ ስለመሆናቸው አስረድተዋል፡፡ በተደረገ ርብርብ በ2015 ዓ.ም 224 ሚሊዮን ብር ተሠብስቦ ገቢ መደረጉንም አንስተዋል፡፡
አንዳንድ ጤና ጣቢያዎች ከቀይ መስቀል፣ እና ከሌሎች የመድኃኒት አቅራቢዎች ጋር የ3ኛ ወገን ውል በመውሰዳቸው ችግሩ እየተቀረፈ ነው ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የጤናው ጉዳይ የራሴ ነው ብሎ እንዲያስብ ለማድረግም የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን አቶ ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡ ሥራው በጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች ሥራ አመራር ቦርድ እየተገመገመ እየተሠራ በመኾኑም ሲጀመር ከነበረው አፈጻጸም አሁን የተሻለ ኾኗል ብለዋል፡፡
እያንዳንዱ ሰው በዓመት ሁለት ጊዜ ጤና ተቋማት ላይ በመገኘት የጤናውን ሁኔታ መከታታል እንዳለበትም አሰገንዝበዋል፡፡ ነገር ግን የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማነስ የጤና መድኅን ክፍያ 0 ነጥብ 4 ብቻ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ በተፈጠረው ግንዛቤ የጤና መድኅን ክፍያ ወደ 1 ነጥብ 8 ከፍ ማለቱን ምክትል መምሪያ ኀላፊው ነግረውናል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!