
ባሕር ዳር :መጋቢት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በቀጣይ ዋናው የቤት ሥራችን እንደመሪ ፓርቲ ነፃነትን በአግባቡ መጠቀምና ማስተዳደር ላይ መስራት ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡
“ድሎችን ማፅናትና ፈተናዎችን መሻገር” በሚል መሪ ሐሳብ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የውይይት መድረክ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡
በመድረኩ በወቅታዊና ታሪካዊ የአመራር ተልዕኮ፣ በሀገራዊ ሰላም፣ ጸጥታ እና የልማት ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋናው ጽሕት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ከተሳታፊ አመራሮች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የኑሮ ውድነትን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ መንግሥታዊ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮችን በሚመለከት ብልጽግና ፓርቲ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ብልፅግና ፓርቲ አስቀድሞ የጀመራቸውን መርህን መሰረት ያደረጉ ተቋማዊ አሰራሮችን አጠናክሮ በማስቀጠል የፓርቲውን ሕዝባዊ ቅቡልነት ማሳደግና ጠንካራ መንግሥታዊ አቅም መፍጠር እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
ይህንንም ለማጠናከር አመራሩ የአመለካከት እና የተግባር አንድነቱን በማጠናከር በኅብረ ብሔራዊ አንድነት በተሰናሰለ ወጥ ሀገራዊ እሳቤ አቅም መሆን እንደሚገባ አንስተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካዊ እሳቤዎች ኢትዮጵያዊ መሰረት ያላቸውና የሀገራችንን እና የህዝባችንን ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ማሳደግና የሕዝቡን ፖለቲካዊ ሞጋችነትና የልማት ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ብልጽግና ፓርቲ መላ መዋቅራዊ አቅሙን ፈትሾ የሚታዩ የአመራር የአቅም ጉድለቶችን አርሞ፣ ውስጣዊ ብልሽቶችን አክሞና መርህን መሰረት ባደረገ አግባብ ተግባራት በማሳለጥ የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥና ዕድገት በማስቀጠል ሕዝባዊ ቅቡልነትን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንደሀገር የመጣውን ነፃነት ከመጠቀም ጋር ሰፊ ክፍተት እንዳለና ነፃነትን ማስከበር በሚመለከት ብልፅግና ፓርቲ የሚደራደርበት ጉዳይ እንዳልሆነ አሳስበዋል፡፡
እንደመሪ ፓርቲ ነፃነትን በአግባቡ መጠቀምና ማስተዳደር ላይ መስራት እንደሚገባም ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
በተመሳሳይ ነፃነትን በፓርቲው ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባና የፓርቲው አመራርና አባል ተገቢ ነፃነት ተጎናፅፎ ሐሳቡን ያለተፅዕኖ እያራመደ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
እንደሀገር የዴሞክራሲ፣ የፍትሕና የዳኝነት ተቋማት በነፃነትና በገለልተኝነት ሥራቸውን አጠናክረው መስራት እንደሚገባቸውም ለተሳታፊ አመራሮች ማንሳታቸውን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!