“በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ለሠላም መሥራት ቅድሚያ የሚሰጠው ዓብይ ጉዳይ ነው” በሠላም ሚኒስቴር የሀገር ግንባታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አስማ ረዲ

121
ባሕር ዳር :መጋቢት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዘላቂ ሠላምን ማረጋገጥ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ከሚጠበቁ መሠረታዊ ለውጦች ውስጥ ቁልፉ እና ቀዳሚው ጉዳይ ነው፡፡ ሠላም የሚገነባውም ኾነ ሠላም የሚፈርሰው በሰው ልጅ አዕምሮ ውስጥ ነው፡፡ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚጸና፣ ፈተናዎችን የሚቋቋም እና ታላቅ ሀገር ለመገንባት የሠላም እሴትን በትውልድ ውስጥ ማስረጽ ዘላቂ ሠላምን ለማምጣት ያግዛል፡፡
ሀገራዊ ሠላምን ለማረጋገጥ ከግለሰባዊ ጥረት እስከ ቤተሰባዊ ስሪት፣ ከማኀበረሰባዊ መሻት እስከ ሕዝባዊ ትጋት፣ ከሃይማኖት አባቶች አስተምህሮ እስከ መንግሥት የፖሊሲ እና ስትራቴጂ አፈጻጸም የሁሉንም ዜጋ ቀና ትብብር ይጠይቃል፡፡ ሀገራዊ ሠላምን ለማረጋገጥ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቢኖሩም የዘላቂ ሠላም ባለቤቱ ግን ሕዝብ እንደኾነ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡
ሠላም ሚኒስቴርም በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ለሠላም መሥራት ቅድሚያ የሚሰጠው ዓብይ ጉዳይ ነው ብሏል፡፡ በሠላም ሚኒስቴር የሀገር ግንባታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አስማ ረዲ ኢትዮጵያ ለዘመናት በዘለቀው የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቷ ውስጥ ሠላሟን የሚፈትኑ ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች አጋጥመዋት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አሁንም ድረስ ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች ዜጎቿን እየፈተኑ ነው ብለዋል፡፡
በሀገራዊ ሠላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የማይተካ ሚና ካላቸው ባለድርሻ አካላት መካከል የሃይማኖት ተቋማት እና የእምነት አባቶች ቀዳሚዎቹ ናቸው ያሉት መሪ ሥራ-አስፈጻሚዋ ከሃይማኖት ተቋማቱ እና ከእምነት አባቶች ጋር በጋራ መሥራት ዘላቂ ሀገራዊ ሠላምን ለማረጋገጥ ይረዳል ነው ያሉት፡፡
የሃይማኖት ተቋማቱ የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ሠላም የማረጋገጥ ሂደት በብቃት እንዲወጡ በእምነት ተቋማት መካከል ያሉ አለመግባባቶችን ማጥበብ፣ ውስጣዊ ችግሮቻቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ ማገዝ እና ጥያቄዎቻቸውን መመለስ ተገቢ ነውም ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ጥንታዊ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ የላቀ ሚና ከነበራቸው ቁልፍ ባለድርሻ አካላት መካከል የሃይማኖት ተቋማት ግንባር ቀደም ናቸው ያሉት ወይዘሮ አስማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተቋማቱ ውስጥ እየተስተዋሉ የመጡ ችግሮችን በመፍታት በሀገራዊ የሠላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የነበራቸውን የጎላ ሚና ለማስቀጠል ይረዳል ብለዋል፡፡
ወይዘሮ አስማ የሃይማኖት ተቋማቱ የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ የሠላም ግንባታ ሂደት በአግባቡ እንዲወጡ መጀመሪያ የተቋማቱ ውስጣዊ ሠላም መረጋገጥ እንዳለበት ገልጸው ለስኬቱም በመቀራረብ መሥራት እና መነጋገር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ሠላም ሚኒስቴርም እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡ በሃይማኖት ተቋማቱ የሚነሱ የሠላም ችግሮች ከተፈቱ ሀገራዊ ሠላምን የማረጋገጡ ሂደት ፈር የሚይዝ እና ቀላል ሂደት ይኾናል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየወባ ወረርሽኝን ለመከላከል 19 ነጥብ 6 ሚሊዮን አጎበር ተሰራጭቷል።
Next article“በቀጣይ እንደመሪ ፓርቲ ነፃነትን በአግባቡ መጠቀምና ማስተዳደር ላይ መስራት ይገባል” አቶ አደም ፋራህ